አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 9 ወራት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ 5 ሺህ 856 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች 97 ነጥብ 7 በመቶዎቹ ምላሽ መሰጠቱን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ሶካ ገለጹ።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን የገለጹት የአስተዳደሩን የ2014 በጀት ዓመት የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት ነው።
ባለፉት 9 ወራት የተከሰቱት የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ካለፈዉ የ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የጥቃት መጠኑ በአራት እጥፍ (400 በመቶ) መጨምሩን ነዉ ይፋ ያደረጉት።
በኢትዮጵያ ከተሰነዘሩ ጥቃቶች መካከል ከፍተኛዉን ቁጥር የያዘዉ የደረ-ገጽ ጥቃት ሲሆን ፥ በመቀጠልም በአጥፊ የማልዌር ጥቃት፣ የመሰረተ ልማት አገልግሎት ማቋረጥና የኦንላይን ማጭበርበር እንደ ቅደም ተከተላቸዉ ከፍተኛ ጥቃት ያስተናገዱ መሆናቸዉን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።
የጥቃቶቹ ዋና ግብም የጂኦፖለቲካል ፍላጎት ባላቸዉ ሃገራት (ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዙ)፣ ከ6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ ምርጫውን ለማደናቀፍ ፍላጎት ያላቸው አካላት፣ ኢትዮጵያ ባካሄደችዉ የህግ ማስከበር እና የህልዉና ዘመቻ ጋር በተያያዘ የፖለቲካ ፍላጎት ባነገቡ አካላት እንዲሁም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ታሳቢ በማድረግ የተሞከሩ ጥቃቶች ናቸዉ።
ጥቃቶቹ የአገር ወሳኝ መሰረተ ልማቶች ኢላማ ያደረጉ እንደሆኑ መገለጹን ከአስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከእነዚህ መካከልም የፋይናንስ ተቋማት፣ የመንግስት ቁልፍ መሰረተ ልማቶች፣ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ድረ-ገጾች፣ ሚዲያዎች በእነዚህ ጥቃት ኢላማ ዉስጥ የወደቁ እንደነበር አቶ ሰሎሞን ሶካ ለዉጭ ጉዳይ እና የሰላም እና ደህንነት ቋሚ ኮሚቴ የ9 ወራት የስራ አፈጻጸም ባቀረቡበት ወቅት ጠቁመዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡