Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት ትሠራለች- ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ የዘለቀውና በመልካም ጉርብትና ላይ የተመሠረተው የኢትዮጵያ እና ኬንያ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለቀጠናው ሀገራት አርዓያ ነው ሲሉ የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ተናገሩ፡፡
የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኬንያ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለምን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት÷ ከአፍሪካ የጋራ መከላከያ ስምምነት የተፈራረሙ ሀገራት የሆኑት ኢትዮጵያ እና ኬንያ በዲፕሎማሲ ዘርፍ በተለይም በኢኮኖሚ ትስስር፣ በቀጠናዊ ውህደት ፕሮጀክቶች እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ያላቸው ትስስር የበለጠ መጠናከሩን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የኬንያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ ናት ያሉት ፕሬዚዳንት ኡሁሩ÷ ኬንያም ኢትዮጵያ ችግር ባጋጠማት ጊዜ ሁሉ እንደዚህ ቀደሙ ሁሉ ከጎኗ እንደምትቆም አረጋግጠዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል በኢኮኖሚው መስክ፣ በመሠረተ ልማት ትስስር፣ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት ዘርፎች የተጀመሩ ትብብሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
አምባሳደር መለስ በበኩላቸው የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በማሳደግ ረገድ የፕሬዚዳንቱ የአመራር ሚና የጎላ መሆኑን ገልጸው፥ በኬንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መብታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ አስተዳደራቸው ላበረከተው ጉልህ አስተዋፅኦ ፕሬዚዳንት ኡሁሩን አመስግነዋል።
በሀገራቱ መካከል ለዘመናት የዘለቀው የመሪዎች ቅርብ ግንኙነት እና የሕዝቦች ወዳጅነት መገለጫ የሆኑት የላሙ ወደብ ፕሮጀክት፣ የሞያሌ የአንድ መስኮት የኬላ አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ የኬንያ ባለሀብቶች ኢንቨስትመንት እያደገ መምጣት እና ኢትዮጵያውያን ቢዝነሶች ወደ ኬንያ ገበያ መግባት የሀገራቱን ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ቀጣይነት የሚያረጋግጡ እና ለሌሎች የቀጠናው ሀገራት አርዓያ የሚሆኑ ለውጦች መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡
በኃይል ሽያጭ ስምምነት እና በቀጠናዊ ሠላምና ፀጥታ ያሉ ትብብሮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም አምባሳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ፕሬዚዳንት ኡሁሩ በኬንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ኬንያ ውስጥ እንደ አገራቸው በነፃነት እንዲኖሩ እፈልጋለሁ ማለታቸውን በኬኒያ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
Exit mobile version