Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

81ኛውን የአርበኞች መታሰቢያ ቀን ስናከብር የድሉን ትሩፋቶች በማጉላትና ለትውልድ በማስተላለፍ መሆን አለበት – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዘንድሮን የአርበኞች መታሰቢያ ቀን ስናከብር የድሉን ትሩፋቶች በማጉላትና ለትውልድ በማስተላለፍ መሆን ይኖርበታል ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት 81ኛውን የኢትዮጵያ አርበኞች የድል ቀን በዓል አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷ ኢትዮጵያ ጠላቶቿ የተኙላት ጊዜ ባለመኖሩ በታሪኳ በርካታ ጦርነቶችን ማካሄዷን ገልጾ÷ ኢትዮጵያ በታሪኳ ጦርነት ፈልጋ እና ተመኝታ እንዲሁም የሌላውን ሉዓላዊነት ጥሳም ሆነ ወረራ ፈፅማ እንደማታውቅ አብራርቷል፡፡

ሁልጊዜም የራሷ በሆነው ሀብት ወይም ሌላ ጉዳይ በጠላቶቿ ትጠቃለች፤ ሆኖም ግን ሁሉንም ጦርነቶች በአሸናፊነት አጠናቃለች ብሏል መግለጫው፡፡

ጦርነቶቹን ያሸነፈቻቸው በጠላቶቿ ድክመት ወይም በታጠቀቻቸው ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ብልጫ ሳይሆን÷ ፡ ሁልጊዜም ጠላት ሲመጣ በሚሰባሰቡትና ጠላትን በአንድነት በሚመክቱት ጀግኖች ልጆቿ መሆኑንም አመላክቷል፡፡

ሁልጊዜም ኢትዮጵያ በጠላቶቿ ስትነካ ትዕግስት የሌላቸው  ውድ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በደምና በአጥንታቸው የአገራቸውን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ሳይደፈር አስከብረው ማቆየታቸውም  ተገልጿል፡፡

በታሪክ ሁልጊዜ ከሚታወሱት የጀግንነት ታሪካችን አንዱ ከስምንት አስርት-ዓመታት በፊት ለአገር ክብርና ለሕዝቦች ነፃነት የአባት አርበኞች የፈፀሙት ገድል መሆኑን ያነሳው መግለጫው÷ በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል የተደረገው የአድዋ ጦርነትና ጦርነቱ በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት መፈፀሙ በወራሪዎች ዘንድ ከፍተኛ የውርደት ስሜትና ፀፀት አስከትሏል ብሏል፡፡

ሽንፈቱም በወቅቱ የበቀል ስሜትን በመቀስቀሱ የአገዛዝና የአስተሳሰብ ለውጥ ማስከተሉን መግለጫው አመላክቷ፡፡

ከለውጦቹ መካከል የፋሽስታዊ አስተሳሰብ መወለድና የመሪው ቤኒቶ ሙሶሎኒ የመንግስት ስልጣን መቆናጠጥ አንዱ መሆኑን የጠቆመው መግለጫው፥ ይህ ፋሽስታዊ ብሔርተኝነትና መሪው እንደ ግብ ከያዘው በዋናነት የሚጠቀሰው ኢትዮጵያን ዳግም በመውረር ከሽንፈቱ ድባቴ በመላቀቅ የጣሊያንን ታላቅነት መመለስ የሚል ነበር ብሏል፡፡

በዚህ መሰረት ከ40 ዓመት የአድዋ ድል በኋላ ፋሽስታዊ አገዛዙ በፈረንጆቹ ጥቅምት 1935 ዓ.ም ኢትዮጵያን መውረሩን አስታውሷል መግለጫው፡፡

በወቅቱ የጠላት ጦር በያዘው የጦር መሳሪያና በሰለጠነ የወታደር የበላይነት ምክንያት ለጊዜውም ቢሆን የወገን ጦርን ቢበትንም÷ ለባርነትና ለጠላት እጅ መስጠት የማያውቁ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን በማደራጀት በአዲስ መልክ በጠላት ላይ መነሳታቸውን መግለጫው አመላክቷል፡፡

ቀያቸውንና ንብረታቸውን ትተው ዱርና ገደሉን ቤታቸው አደረጉ፤ እንደ ስሙ የአንበሶች ስብስብ የሆነ ‘የጥቁር አንበሳ’ የተሰኘውን የአርበኞች ስብስብ መሰረቱ ብሏል፡፡

አርበኞቹ በመላ ኢትዮጵያ በብሔርና በቋንቋ ሳይለያዩ በሁሉም አካባቢዎች በመደራጀትና በመንቀሳቀስ ጠላትን እንቅልፍ ማሳጣታቸውን ገልጾ÷ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት ጠላትን እረፍት በመንሳት በፈረንጆቹ ግንቦት 5 ቀን 1941 ዓ.ም አርበኞቹ የነፃነት ታጋዮች በጠላት ላይ ድል መቀዳጀታቸውን አንስቷል፡፡

ለአምስት ዓመታት አገር ለቀው ውጭ አገር በስደት የቆዩት ንጉሱም በድል ወደ አገራቸው ተመለሱ፤ ዕለቱም እስከ ዛሬ ድረስ የአርበኞች የድል ቀን በመባል ይከበራል ብሏል መግለጫው፡፡

ጀግኖች አርበኞችም ለአገራቸው ክብርና ለሕዝቦቿ ነፃነት ላደረጉት ተጋድሎ በየዓመቱ ሚያዝያ 27 ቀን ይወደሳሉ፤ ይታወሳሉ፤ ለዘለዓለም በትውልድ ሲወደሱም ይኖራሉ ብሏል፡፡

የዘንድሮውን 81ኛው ዓመት የአርበኞች መታሰቢያ ቀን ስናከብር የድሉን ትሩፋቶች በማጉላትና ለትውልድ በማስተላለፍ መሆን ይኖርበታል ያለው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ÷ ኢትዮጵያ ከሩቅና ከቅርብ በታሪካዊ ጠላቶቿ ስትጠቃና ስትወረር ዛሬ ላይ መድረሷን ገልጿል፡፡

ምንም እንኳን ፈልጋ የሰውን አገር ወራ ባታውቅም ጠላቶቿ አልተኙላትም፤ አይተኙምም ብሏል፡፡ ሆኖም ግን በሕዝቦቿ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትና በአልገዛም ባይነት ወኔያቸው ሉዓላዊነቷና የሕዝቦች ነፃነት ተጠብቆ ይቀጥላል ብሏል አገልግሎቱ፡፡

ዛሬም አገራችን ከቅርብና ከሩቅ ታሪካዊ ጠላቶቿ በሚሰነዘርባት ሁለንተናዊ ጥቃት ሳትንበረከክ ልጆቿ ከአባቶቻችን በወረሱት የአገር ፍቅር ለሕዝቦች ክብርና ለአገር አንድነት ዘብ ቆመዋል፡፡ መጪው ትውልድም ለጋራ አገሩና ለክብሩ በአንድነት በመቆም ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ እንደሚያሸጋግራት ጥርጥር የለውም ነው ያለው፡፡

የፋሽስቱ አገዛዝ እንደ ወሳኝ የማሸነፊያ መሳሪያ ተማምኖ የነበረው በታሪክ “ፋሺዝም” ተብሎ የሚታወቀውን ጫፍ የረገጠ ፅንፈኝነትና አክራሪነትን መሆኑን ገልጾ÷ ትውልዱ ፅንፈኝነትና አክራሪነት ራሱን በልቶ የሚያጠፋ አስተሳሰብ መሆኑን ከፋሺስታዊ አገዛዙ በመማር ከዋልታ ረገጥ አስተሳሰብ በመላቀቅ አገሩን ማፅናት ይጠበቅበታል ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በመግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

Exit mobile version