አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 24 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝቦች ህብረብሄራዊ አንድነት መገለጫ ፤ የሃይማኖቶች መከባበርና የመቻቻል ተምሳሌት በሆነችው አዲስ አበባና በመላው ሃገራችን የህዝቦችን ሰላም ለማደፍረስና አንድነታችንን ለመበተን በሚፈልጉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ቅንጅት የተለያዩ የጥፋት እቅዶች ለመተግበር እየሰሩ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል።
እነዚህ ድርጊቶችም ከሰሞኑ በተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች መታየታቸው ይታወሳል፡፡
በዛሬው እለትም ታላቁን የኢድ ሰላት ለማከናወን ህዝበ ሙስሊሙ ከየአካባቢው በመምጣት በአዲስ አበባ ስታዲየም እና በዙሪያው በተሰባሰበበት ወቅት ይህንኑ እኩይ ሴራቸውን ለመተግበር ምዕመኑ በተረጋጋ ሁኔታ ስርዓቱን እንዳያያካሂድና ወደ ትርምስና ብጥብጥ ለመክተት ሙከራ ተደርጓል፡፡
የዚህ እኩይ ተልእኮ ውጥን በሰማዕታት ሃውልትና በመስቀል አደባባይ በተደረገ ሙከራ በንብረት እና በፀጥታ ሃይሎች ላይ ከደረሰው መጠነኛ ጉዳት ቢያይደርስም በሰላም ወዳድ ሙስሊም ወገኖቻችን ብርቱ ጥረትና በፀጥታ ሃይሎች ቅንጅት የትርምስ ፍላጎቱና ዕቅድ ሙሉ ለሙሉ ከሽፏል፡፡
እንዲሁም ህዝበ ሙስሊሙም በሁሉም አካባቢዎች ሶላቱን ፈፅሞ ወደየአካባቢውና ወደየቤቱ በሰላም ተመልሶ ገብቷል፡፡
መንግስትም የተፈጠረው የፀጥታ መደፍረስ ከተከሰተበት ሰዓት አንስቶ የችግሩን መንስኤ ለማወቅና አጥፊዎችን ለይቶ ለህግ ለማቅረብ አስፈላጊውን የማጣራትና የክትትል ስራ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ስለሆነም መላው የከተማችን ነዋሪ ለዘመናት የዘለቀውን አንድነታችን እንዲሁም ውብ ሃይማኖታዊ እሴቶቻችንን ገፅታ ለማበላሸትና እርስ በእርስ ለማባላት የሚታቀዱ እኩይ አላማዎችን መሆናችውን ከወዲሁ በመረዳት የእነዚህን ሃይሎች ሴራ እንዲያጋልጥና እንዲያከሽፍ ጥሪያችንን እናቀርባለን::
እንዲሁም ከመንግስት ጎን ሆኖ አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን ብሎም እንደተለመደው አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅና የጀመርነውን ሃገራችንን ብሎም ከተማችንን የመቀየር ጥረት አጠናክረን እንድንቀጥል ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር