አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በአማራ ክልል በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ኢንተርፕራይዞች እና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት 187 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል።
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ÷ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የክልል ቢሮዎችን፣ ኮሌጆችን እና ተጠሪ ተቋማትን በማስተባበር በአማራ ክልል በጦርነት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው በሥራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ ሥር ለሚገኙ ተቋማት ድጋፍ ሲያሰባስብ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ በኮምቦልቻ ከተማ ለቴክኒክና ሙያ ተቋማት የተደረገው ድጋፍ እና የደብረብርሃን ሆስፒታልን አገልግሎት ለማሳደግ መለስተኛ የማስፋፊያ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ÷ ሚኒስቴሩ ጉዳት ለደረሰባቸው ቴክኒክና ሙያ ተቋማት እና ኢንተርፕራይዞች በተለያዩ ጊዜያት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል ።
ስንተባበር ኢትዮጵያን ማፅናት እንችላለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ የአማራ ክልል ህዝብ እንደ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አይዟችሁ የሚሉ ተቋማትን ድጋፍ ስንቅ አድርጎ አይበገሬ ሆኖ ይቀጥላል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የአማራ ክልል ሥራና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አረጋ ከበደ በበኩላቸው ÷በጦርነቱ 8 ዞኖች እና አንድ ከተማ አስተዳደር ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በጦርነቱም በአጠቃላይም በዘርፉ ከ13 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ውድመት መድረሱን ገልፀው÷ለመልሶ ግንባታም ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።