ዓለምአቀፋዊ ዜና

ቻይና በዜጎቿ ሥነ-ልቦና የተቃኙ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ዩኒቨርሲቲዎችን ዕውን ልታደርግ ነው

By Alemayehu Geremew

April 26, 2022

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ÷ የሀገሪቷ ዩኒቨርሲቲዎች ሥርዓተ-ትምህርት ከዜጎቻቸው ጥልቅ ሥነ-ልቦናዊ ዕሳቤዎች የተቀዱ መሆን እንዳለባቸው አሳሰቡ፡፡

በትናንትናው ዕለት ቤጂንግ በሚገኘው ሬንሚን ዩኒቨርሲቲ በነበራቸው የጉብኝት መርሃ-ግብር ላይ የቻይና ዩኒቨርሲቲዎች የውጭ ሀገራትን ሥርዓተ-ትምህርት የልኬት ደረጃ እና ሞዴል መኮረጅ እንደሌለባቸው እና የዜጎቻቸውን ሥነ-ልቦና መሠረት ያደረገ ትምህርት መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የሀገሪቷ ዩኒቨርሲቲዎች ቻይና ያለፈችባቸውን የአመራር ርዕዮቶች ለተማሪዎቻቸው ማስተላለፍ እንዳለባቸውም አስምረውበታል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ቤጂንግ በሚገኘው ሬንሚን ዩኒቨርሲቲ የተገኙት በፈረንጆቹ ግንቦት አራት ከሚከበረው የሀገሪቷ “የወጣቶች ቀን” ቀደም ብለው እንደሆነ ሲ ጂቲ ኤን ዘግቧል፡፡

በቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ስም በሀገሪቷ ለሚገኙ ወጣቶች ሁሉ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋልም ነው የተባለው፡፡

ዢ ጂንፒንግ በፈረንጆቹ 2018 በቻይና ፔኪንግ ዩኒቨርሲቲ የ120ኛ ዓመት ክብረ – በዓል ላይ ተገኝተው ከውጭ ሀገራት እና ከሀገሪቷ ተማሪዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር መወያየታቸው ይታወሳል፡፡