Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለ2014/15 የመኸር ምርት የማዳበሪያ እጥረት አያጋጥምም – ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) ለ2014/15 የምርት ዘመን የመኸር ምርት የማዳበሪያ እጥረት ሊያጋጥም እንደማይችል የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

የሚኒስቴሩ የስራ ሃላፊዎች በወቅታዊ የማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት ላይ ውይይት አድርገዋል።

በውይይታቸውም ለመኸር ወቅቱ 15 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ የሚያስፈልግ ሲሆን ፥ 12 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ግዢው ተፈጽሟል ያሉት በሚኒስትሩ የግብይት አቅርቦትና ስርጭት ዳይሬክተሩ አቶ መንግስቱ ተስፋ ናቸው።

ከባለፈው ዓመት ያደረገ 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታልና ጅቡቲ ላይ የደረሰውን 4 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታሉን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት 6 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በተጨባጭ መኖሩንም ነው የኤክስቴንሽን ዳይሬክተሩ አቶ ግርማሜ ጋሩማ የተናገሩት።

ዘንድሮ በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋው መጨመሩን የሚናገሩት የስራ ሃላፊዎቹ ፥ ዓለም አቀፍ ሁኔታ ምክንያት መሆኑን ነው በማሳያ የሚናገሩት።

ግዢያቸው የተጠናቀቁትን ቀሪ ማዳበሪያዎችንም በአጭር ጊዜ አጓጉዞ ለማስገባት ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተሰራ ነው።

ከዋጋ ውድነት በተጨማሪ ስርጭት ላይ የሚፈጠር ክፍተት እንዳይኖርም ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከአፈር ማዳበሪያ ጥገኝነት ለመላቀቅም ለተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የአፈር ለምነት ማሻሻያ ዳይሬክተሩ አቶ ተፈራ ሰለሞን ተናግረዋል።

የአፈር ለምነትን ሊያሻሽሉ የሚችሉ እድሎችን በሙሉ በጥናት በማስደገፍ ስራ ላይ እያዋልን ነውም ብለዋል።

በትዕግስት ስለሺ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version