አዲስ አበባ ፣ የካቲት 21፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የኪነጥበብ ባለሙያዎች እና ከያኒያን በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ የቱሪስት መዳረሻ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ፕሮጀክቶቹን ለኪነጥበብ ባለሙያዎች ባስጎበኙበት ወቅት እንደገለጹት ኪነ ጥበብ ማህበረሰቡን እርስ በርሱ የማስተዋውቅ እና የማስተሳስር ኃይል አለው ።
በጠላትነት የሚፈላለጉ አካላትን በምትሃታዊ ሙዚቃ እጅ ለእጅ ተያይዘው ልባቸውን ለፍቅር ይከፍታሉ ሲሉ ገልፀዋል ።
ከኪነ ጥበብ ከያንያን ጋር በመሆንም የከተማ አስተዳደሩ የሚሰራቸውን ስራዎች በባለቤትነት መንፈስ በጋራ ለመስራት እና ተሳትፎ ለማድረግ መነጋገራቸውን ኢንጅነር ታከለ ኡማ ተናግረዋል ።
የኪነጥበብ ባለሙያዎቹ በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ እና የከተማዋን የቱሪዝም እድገት በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋሉ የተባሉ የእንጦጦ እና ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝቱ የተሳተፉ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ ከተማዋን ገጽታ ለመቀየር እና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የሚያደርገው እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን ገልጸው በኪነ ጥበብ ስራዎቻቸው አስተዳደሩን ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን በጉብኝቱ ወቅት መናገራቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሪታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።