አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕላን ኢንተርናሽናል የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት በድባጤ ወረዳ በፀጥታ ችግር ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች ግምታቸው 9 ሚሊየን 849 ሺህ 130 ብር ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቋል።
የፕላን ኢንተርናሽናል ድርጅት የሕፃናት ጥበቃ ኦፊሰር አቶ አስማማው ተስፋዬ÷ በመተከል ዞን በድባጤ ወረዳ የተፈናቀሉ የማህበረሰብ ክፍሎች የገጠማቸውን የቁሳቁስ ችግር ለመቅርፉ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በመተከል ዞን በአምስት የተፈናቃይ ማዕከሎች ድባጤ፣ ወንበራ፣ ቡለን፣ ማንዱራ እና ዳንጉር ወረዳዎች ላይ ምግብነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች እያሰራጨ መሆኑንም አሰተባባሪው ገልጸዋል።
በዚህም በድባጤ ወረዳ ብቻ 1ሺህ 400 ለሚሆኑ አባወራ እና እማ ወራዎች ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ማሰራጨቱን አብራርተዋል፡፡
በቀጣይ ከአጋር አካላት ፈንድ በማፈላለግ ተፈናቃይ የሆኑ ወገኖች ወደ ቀያቸው እሰኪመለሱ ድረስ የተጀመረው ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ መግለጻቸውን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖች በበኩላቸው÷ መንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ላደረጉላቸው ድጋፍ አመስግነው÷ በቀጣይ የሰብዓዊ ድጋፍ በወቅቱና በተገቢው መንገድ እንዲደርስላቸው ጥሪ አቅርበዋል።
መንግስት በፀረ ሰላም ኃይሎች ላይ የጀመረውን የሕግ ማስከበር እርምጃ ተግባራዊ በማድረግ ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ወደ ቀያቸው ተመልሰው መደበኛ የግብርና ሥራ እንዲጀምሩ ጠይቀዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!