አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ ምክንያት እርዳታ የሚሹ ችግሮችን ለማለፍ እንደ ቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን አይነት ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ትብብር እንደሚያስፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ ፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን ከቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የዓለም አቀፍ የልማት ተቋም ፕሬዚዳንት ክርስቶፈር ኤሊያስ ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።
በውይይታቸው የቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ እያከናወናቸው ያሉ የልማት ስራዎችን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የመከሩ ሲሆን፥ በወቅቱም አቶ ደመቀ መኮንን ፋውንዴሽኑ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ባከናወናቸው የልማት ተግባራት ቁልፍ አጋርነቱን በተግባር እንዳሳየ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በተለይ በትምህርት፣ በጤና እና ግብርና ዘርፎች እያደረገ ያለውን አስተዋፅኦ አድንቀው ዘርፎቹን ለማሻሻል መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አቶ ደመቀ ጦርነት እና ድርቅ በኢትዮጵያ ያስከተላቸውን ወቅታዊ ፈተናዎች ያብራሩ ሲሆን÷ በጦርነት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ድርቅ በተለይም በደቡባዊ ምስራቅ የኢትዮጵያ ክፍል ብዙ ጉዳት ማድረሱን ገልፀው በአጠቃላይ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ እርዳታ የሚሹ 24 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎችን ለመርዳት መንግስት ብዙ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል ።
የቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ግሎባል ዴቨሎፕመንት ቪዥን ፕሬዚዳንት ክርስቶፈር ኤሊያስ በበኩላቸው÷ ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ቁልፍ በሆኑ የልማት መስኮች የሚያደርጋቸውን ድጋፎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የተሻለ የልማት አስተዋፅኦ ለማበርከት መንግስት ትኩረት በሚሰጣቸው ዘርፎች ላይ ትብብር እና ድጋፋቸው እንደሚቀጥልም አውስተዋል።
አያይዘውም በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የግብርና ግብዓቶች እና የማዳበሪያ ዋጋ መናሩን ጠቅሰው ጫናውን ለመቋቋም እንዲሁም ክፍለ ኢኮኖሚውን ለማዘመን የሚሰሩ ስራዎችን የቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን እንደሚደግፍ በውይይቱ ላይ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡