Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ኤሌክትሪክ ሽቦ የሰረቁ ተከሳሾች በጽኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የተዘረጋ የኤሌክትሪክ ሽቦ ቆርጠው የሰረቁ ሁለት ተከሳሾች በጽኑ እስራት መቀጣታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ተከሳሽ ፀጋዬ ቴዎድሮስ እና ያብስራ ተስፋዬ ፥ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32(1)ሀ እና የቴሌኮሙኒኬሽንና የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማት አውታሮችን ደህንነት ለመጠበቅ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 464/2005 አንቀጽ 4 ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ መቆየቱ ተገልጿል፡፡
የሁለቱን ተከሳሾች ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ጥፋተኝነታቸውን በማስረጃ በማረጋገጥ እና ጥፋተኞችን ያርማል ሌሎችንም ያስጠነቅቃል በማለት ፀጋዬ ቴዎድሮስ በ7 ዓመት ከ8 ወር ጽኑ እስራት እንዲሁም ያብስራ ተስፋዬ በ7 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡
ተከሳሾቹ በየካቲት ወር 2013 ዓ.ም በግምት ከሌሊቱ 7 ሰዓት አካባቢ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው ልደታ ቤተክርስቲያን ባቡር ፌርማታው አካባቢ ወንጀሉን እንደፈጸሙ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ንብረትነቱ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት የሆነ 40 ሜትር ርዝመት እና 80 ሺህ ብር የዋጋ ግምት ያለውን የባቡር የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ ሽቦ ቆርጠው መውሰዳቸውን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን አስቀድሞ ለመከላከል እና ከተፈጸመ በኋላ አጥፊዎች በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲል የአዲስ አበባ ፖሊስ መልእክቱን አስተላልፏል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version