አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አርሶ አደሩ ያለበትን የምርጥ ዘር ችግር የሚያቃልል የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት ማዕከል ስራ ጀምሯል፡፡
ኬምቴክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ በ500 ሄክታር የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት ስራን የጀመረ ሲሆን፥ ከ40 ሺህ በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የድርጅቱ ባለቤት አቶ ይመኑ ጀምበሬ ገልፀዋል፡፡
በቤንች ሸኮ ዞን በዓመት ከ40 ሺህ ሄክታር በላይ በቆሎ እንደሚመረት የገለጹት የዞኑ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ መስፍን ጉብላ ፥ የምርጥ ዘር ብዜት ማዕከሉ አርሶ አደሩ ያለበትን የግብዓት ችግር ከመፍታት ባሻገር ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፉ በክልሉ ከ250 ሺህ ሄክታር በላይ በቆሎ በየዓመቱ ቢመረትም ከፍተኛ የምርጥ ዘር እጥረት መኖሩን የገለጹ ሲሆን ፥ በክልሉ የመጀመሪያ የሆነው የዘር ብዜት ማዕከል የአርሶ አደሩን ችግር በማቃለል ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡
ስራ የጀመረው የምርጥ ዘር ብዜት ማዕከል በክልሉ ያለውን የዘር ፍላጎት ከ30 እስከ 40 በመቶ ይሸፍናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ተራመድ ጥላሁን