Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኤጀንሲው “ከኢድ እስከ ኢድ ጥሪ”ን ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት ለሚመጡ ተጓዦች የሚያገለግል ጊዜያዊ መመሪያ አወጣ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ”ከኢድ እስከ ኢድ ጥሪ”ን ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት ለሚመጡ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የሚያገለግል ጊዜያዊ መመሪያ አወጣ።
ኤጀንሲው ለኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት በላከው ደብዳቤ እንዳስታወቀው፥ የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት ለሚመጡ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ከቪዛ፣ ካልታደሰ ፓስፖርትና ከትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ ጋር በተያያዘ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ በመስጠት የጥሪው ዓላማ እንዲሳካ ጊዜያዊ መመሪያው መዘጋጀቱን ገልጿል።
በተያያዘ ” ከኢድ እስከ ኢድ ወደ ሀገር ቤት” ሀገራዊ ጥሪን ተቀብለው ለሚመጡ ከቪዛ፣ ያልታደሰ ፓስፖርት እና ከትውልድ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ ጋር የተያያዘ ያወጣውን ጊዜያዊ መማሪያ በውጭ ያሉ ኤምባሲዎች በመገንዘብ ዳያስፖራዎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንዲቻል ጊዜያዊ መመሪያ ማውጣቱን አስታውቋል፡፡
ያልታደሰ ፓስፖርትና የትውልድ መታወቂያ ጋር በተያያዘ ፥አዲስም ሆነ እድሳት የፓስፖርት አገልግሎት በኦንላይን የሚሰጥ በመሆኑ በኦንላይን ያመለከቱ ግለሰቦች ከ15 ቀን ባነስ ታትሞ የሚደርሳቸው ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም ያልደረሳቸው ካሉ ኤምባሲው መታወቂያ ቁጥሩን ከላከ በአስቸኳይ ታትሞ እንደሚላክ ተገልጿል፡፡
ሆኖም የጉዞ ሠነድ የሌላቸው ወገኖች በዚህ ጉዞ ሊስተናገዱ እንደማይችሉ ነው ኤጀንሲው ያስታወቀው፡፡
ከቪዛ ጋር በተያያዘ ፥ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሆኖ የታደሰም ሆነ የአገልግሎት ጊዜው ያለፈበት የትውልደ ኢትዮጵያ መታወቂያ ያላቸው ያለቪዛ ወደ ኢትዮጵያ መግባት የሚችሉ ሲሆን ፥ ጊዜው ያለፈበትም ይሁን ያላለፈበት የትውልደ ኢትዮጵያ መታወቂያ በእጃቸው መያዝ እንደሚኖርባቸውም ተመላክቷል፡፡
በተለያየ ምክንያት ጥገኝነት የጠየቁ እና የሌላ አገር ሰነድ ይዘው ለሚመጡ መንገደኞችም ከኤምባሲው የተጻፈላቸውን ደብዳቤ በማየት እዚያው ደብዳቤ ላይ የገቢ ማህተም ተመትቶ በመዳረሻ እንዲገቡ የሚደረግ ሲሆን ፥ ኤምባሲው በአቅራቢያ የሌላቸው መጥተው በመዳረሻ በተዘጋጀው ካርድ ላይ ገቢ ማህተም ተመትቶላቸው መግባት እንደሚችልም ነው የተገለጸው፡፡
የኤርትራ ፓስፖርት የያዙትም ሆነ የውጭ ዜግነት የጉዞ ሰነድ ያላቸው ኤርትራውያን በልዩ ሁኔታ በኦንላይን ወይም በመዳረሻ ቪዛ እንደሚስተናገሩ ተገልጿል፡፡
በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች የኢድ ዓልን በጋራ ለማክበር ፍላጎት ያላቸው በኤምባሲ የተረጋገጠ ደብዳቤ ከያዙ ብቻ በመዳረሻ ላይ ቪዛ ማግኘት እንደሚችሉ ተመላክቷል፡፡
በጎረቤት ሀገራት የሚገኙ የውጭ ዜጎች በባቡር ወይም በየብስ ኬላዎች የኦንላይን ቪዛ ይዘው ለመግባት የሚመጡ በተቀላጠፈ መልኩ አገልግሎቱ በየብስ የኢሚግሬሽን መቆጣጠሪያ ኬላ እንደሚሰጥም ተገልጿል፡፡
በዓሉን ለመታደም የሚመጡ የሌላ እምነት ተከታዮች ኢትዮጵያውያንም ሆኑ የሌላ ሀገር ዜጎች በተመሳሳይ መልኩ አገልግሎቱን በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እንደሚያገኙ ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ለበለጠ መረጃም በስልክ ቁጥሮች +251929172827፣ 251944720533 ፥ +251944307514 መደወል እንደሚቻል ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version