አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ትልቅ አደራ እና ሃላፊነት አለበት አሉ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁራን፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩና የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ ዶክተር ባምላክ ይደግ÷ብሄራዊ መግባባትን እውን ለማድረግ በሚካሄደው ውይይት የፖለቲከኞች እና የልሂቃን ቁርጠኝነት ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እናተመራማሪዋ ሙሉነሽ ደሴ በበኩላቸው ÷አገራዊ የምክክር ሂደቱ አካታችና አሳታፊ መሆን ለታቀደው ብሄራዊ መግባባት ስኬት ትልቁን ሚና እንደሚጫዎት ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣይ ለምታደርገው ብሄራዊ ምክክርም በሁሉም መስኮች ትምህርት ሊሆኗት የሚችሉ ተሞክሮዎችን ከጎረቤቶቿ ከኬንያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን ፣ቱኒዚያ፣ ሴኔጋል እና ከሌሎችም መቅሰም ትችላለች ብለዋል ምሁራኑ።
እንደ ቤኒንና ሴኔጋልን የመሳሰሉት አካታችነትን በአግባቡ የተገበሩና ሂደቱም በዜጎቻቸው የታመነበት እንደነበር ያነሱት ምሁራኑ÷አብዛኞቹ አገራት አካታችነት ላይ ውስንነት ያለባቸው ስለነበሩ የሚጠበቀውን ውጤት ማስመዝገብ እንዳልቻሉ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከእነዚህ ሁሉ አገራት የተለያዩ ግብዓቶችን በመቀመር እንደ አገራዊ ቁመናዋ እና ማህበሰረባዊ ውቅሯ የምክክር ሂደቱን ስኬታማ ማድረግ እንደሚጠበቅባት አስገንዝበዋል፡፡
የምክክር ሂደቱ ስኬታማ፣ ተዓማኒ፣ ቅቡልና አካታች ይሆን ዘንድም ከመንግስት ጀምሮ ከየትኛውም አካል ተፅዕኖ ነፃ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።
ኢትዮጵያውያን ብሄራዊ መግባባት ላይ ከደረሱ አሁን ያሉባቸውን ፈተናዎች ወደአጋጣሚ የመቀየር አቅም እንዳላቸውም ምሁራኑ ተናግረዋል።
በሙሀመድ አሊ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!