አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ ኢትዮጵያ በሚገኙት ሐረሪ ክልል፣ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ህፃናት የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት በዘመቻ እንደሚሰጥ ተገለጸ።
የ2014 ዓ.ም ሁለተኛው ዙር የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ከሚያዚያ 7 እስከ ሚያዝያ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ቤት ለቤት እንደሚሰጥ ተጠቁሟል ፡፡
በሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ የድንገተኛ ጤና አደጋ ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ቱፋ እንደተናገሩት÷ ለአራት ቀናት በሚሰጠው የክትባት ዘመቻ ለ56 ሺህ 394 ህፃናት ክትባቱን ለመስጠት ታቅዷል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ዩሱፍ ሰኢድ በበኩላቸው÷ የክትባት ዘመቻው በአስተዳደሩ የከተማና ገጠር ቀበሌዎች የሚካሄድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከ78 ሺህ በላይ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን ለመከተብ ዕቅድ መያዙን ነው ያስታወቁት፡፡ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ጤና ጽህፈቤት ሃላፊ አቶ መሐመዲን ከቢር ሁሴን÷ በዞኑ ስር በሚገኙ 20 ወረዳዎችና 4 የከተማ አስተዳደሮች 1 ሚሊየን 235 ሺህ 227 ህጻናትን ለመከተብ መታቀዱን ገልፀዋል።
ለክትባቱ የሚሆኑ መድሃኒቶችና ሌሎች ግብዓቶች መዘጋጀታቸውንና በቤት ለቤት በሚሰጠው ዘመቻ የጤና ባለሙያዎች እና ድጋፍ ሰጪዎች እንደሚሳተፋበት ተመላክቷል።
በተሾመ ኃይሉ