አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 5፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ማዳበሪያ በወቅቱ ለማድረስ የትራንስፖርት ስራው እየተሳለጠ መሆኑን በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋየ ተናገሩ፡፡
በጅቡቲ የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ዛሬ ጠዋት የማዳበሪያ ጭነት በሚስተናገድበት የዶራሉ ሁለገብ ወደብ ተገኝተው ማዳበሪያን የማጓጓዝ ሂደትን ተመልክተዋል፡፡
የእርሻ ወቅት መድረሱን ተከትሎ የማጓጓዝ ሂደቱን ምልከታ ማድረጋቸውን የገለጹት አምባሳደሩ ፥ማዳበሪያ በወቅቱ ለአርሶ አደሮች የሰብል ማዳበሪያ ማድረስ ወሳኝ የኦፕሬሽን ስራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም ማዳበሪያን በወቅቱ እንዲደርስ በትጋት እየሰሩ ላሉ የወደብ አመራሮችና ሠራተኞች አምባሳደሩ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የዶራሌ ወደብ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዲጃማ ኢብራሂም ዳራር እና በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ድርጅት የጅቡቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ታዬ ጫላን ጨምሮ ኦፕሬሽኑን የሚመሩ ከፍተኛ ባለሙያዎች በምልከታው ላይ መሳተፋቸውን ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡