Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ካናዳ በኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት እንደምታግዝ ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት ካናዳ የበኩሏን እገዛ እንደምታደርግ በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ስቴፋኒ ጆቢን ገለጹ።

በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ስቴፋኒ ጆቢን÷የካናዳና ኢትዮጵያ የቆየ ጠንካራ ወዳጅነት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የገጠማትን ወቅታዊ ችግር እንድታልፍ ካናዳ እገዛ እንደምታደርግ አረጋግጠው÷የኢትዮጵያን የተለያዩ የልማት ጥረቶችም ትደግፋለች ብለዋል።

በተለይም ሴቶችን ማዕከል ያደረገው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችንን መሰረት በማድረግ በኢትዮጵያ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን እየደገፍን ነው ያሉት አምባሳደሩ÷በኢትዮጵያ ሴቶችን ያማከለ ጠንካራ ኢኮኖሚ እና የጤና ሥርዓት ለመዘርጋት በሚደረገው ጥረት ካናዳ የበኩሏን እገዛ እያደረገች መሆኑንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሚካሄደው አገራዊ ምክክር ካናዳ በአዎንታዊ ጎኑ የምትቀበለውና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ታምናለች ብለዋል።

አገራዊ ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲመታና በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ሁሉን አቀፍና ግልጽ የፖለቲካ ሂደቶች ሊኖሩት እንደሚገባ ጠቁመው÷ በጦርነቱ ወቅት የተፈጸሙትን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ የተጠያቂነትና የፍትህ ሥርዓት ገቢራዊ ማድረግ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጋር ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተደጋጋሚ የስልክ ልውውጥ ማድረጋቸውን አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ለኢትዮጵያ አቻቸው ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ድጋፍ የወሰነችው የተኩስ አቁም ውሳኔ ተገቢ መሆኑን ገልጸውላቸዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ የካናዳ ዓለም አቀፍ የድጋፍ ትብብር መርኃ-ግብር አንዷ አገር መሆኗን ገልጸው÷ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2021 እስከ 2022 ኢትዮጵያ 43 ሚሊየን የካናዳ ዶላር ድጋፍ እንደተቀበለች ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version