አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2014 ዓ.ም የካዳስተር ምዝገባ እና እወጃ ሥራ እንደሚካሄድ የከተማዋ መሬት ምዝገባና ማረጋገጫ ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ገብሬ ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ ከዚህ ቀደም የመሬት ይዞታቸውን በካዳስተር ያላስመዘገቡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መረጃዎቻቸውን ለሚቀጥሉት ተከታታይ 15 ቀናት ማዘጋጀት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ከ10 ዓመት በፊት ጀምሮ ሕጋዊ የመሬት ይዞታ የማረጋገጥ (ካዳስተር) ሥራ እየሠራ ሲሆን÷ በዚህ ዓመት በመዲናዋ የለሚኩራ ክፍለ ከተማን ሳይጨምር በ10 ክፍለ ከተሞች ውስጥ በሚገኙ 25 ቀጠናዎች ላይ የመሬት ይዞታን የማረጋገጥ እና የእወጃ ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
በዚሁ መሰረት ይዞታ የማረጋገጥ እና የእወጃ ሥራው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2014 ዓ.ም ለአምስት ወራት እንደሚሠራ ተመላክቷል፡፡
በዚህ ወቅት በሕግ ተይዘው ካሉ የመሬት ጉዳዮች እና የሕግ ክርክሮች ውጪ ምንም ዓይት የስም ዝውውር እንደማይካሄድ ነው የተገለጸው፡፡
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጀማል ሃጂ በበኩላቸው÷ከተማ አስተዳደሩ ከ2008 እስከ 2011ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ከ118 ሺህ በላይ የመሬት ይዞታዎችን እና ከ161 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በካዳስተር መመዝገቡን ጠቁመዋል፡፡
የካዳስተር ምዝገባ ሒደቱ ተዓማኒ እንዲሆንም ከማህበረሰቡ የተውጣጡ ታዛቢዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በፈቲያ አብደላ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!