አዲስ አበባ፣ሚያዝያ 4፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአራት ዓመት ሕፃን የሰወሩ ግለሰቦች በእስራት መቀጣታቸውን የሸካ ዞን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የሸካ ዞን ፖሊስ መምሪያ የነፍስ ግድያና የወንጀል ትራፊክ አደጋ ምርመራ አስተባባሪ ዋና ሳጅን ወንድማገኝ አለማየሁ እንደገለፁት ተከሳሾቹ ህዳር 25 ቀን 2014 ዓ.ም ከረፋዱ 5 ሰዓት በሸካ ዞን የኪ ወረዳ የጻኑ ቀበሌ ነዋሪ የሆነችውን የ4 አመት ሕፃን በመሰወር ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።
በዚህም አንደኛ ተከሳሽ መለሰ ተመስገን ሕፃኗን ብስኩት እገዛልሻለሁ በማለት ጠርቶ በመውሰድ በአቅራቢያ ከሚገኝ ሱቅ ብስኩትና ራኒ መግዛቱንና እስከቀኑ ስድስት ሰዓት አቆይቶ ለሁለተኛ ተከሳሽ ታምራት አለሙ አሳልፎ መስጠቱን አስታውቀዋል።
የህፃኗ ቤተሰቦች ለፖሊስ አቤቱታ በማቅረባቸው ፖሊስ በአካባቢው መረጃዎችን ሲያሰባስብ መቆየቱንና ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ ሲያደርግ መቆየቱንም ገልጸዋል።
ዐቃቤ ህግ በሁለቱ ተከሳሾች ላይ ክስ መስርቶ ፍርድ ቤት ያቀረባቸው ሲሆን የሸካ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቴፒ ምድብ ችሎት ግራ ቀኙን ሲያከራክር ቆይቶ፥ ተከሳሾቹን በኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32 (1) ሀ እና በሰው የመነገድና ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀፅ 4 (1) (ሀ) ስር የተደነገገውን ህግ በመተላለፍ ጥፋተኛ ብሏቸዋል።
በዚህም መሠረት የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቴፒ ምድብ ችሎት ሚያዚያ 4 ቀን 2014 ዓ.ም ባስቻለው የወንጀል ችሎት 1ኛ ተከሳሽ መለሰ ተመስገን በ9 አመት ፅኑ እስራትና በ10 ሺህ ብር እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ ታምራት አለሙ በ10 አመት ፅኑ እስራትና 10 ሺህ ብር እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል።
ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ የ4 አመቷ ሕፃን በህይወት አለመገኘቷን የገለፁት መርማሪው አሁን ላይም ፖሊስ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ከዞኑ ፖሊስ መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!