አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በህንድ ሲካሄድ የቆየው የኢንቨስትመንት ፎረም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የሀሪያና ከተማ አስተዳደር የውጭ ጉዳይ መምሪያ በተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ተጠናቋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳንኤል ተሬሳ በሀሪያና ከተማ በኩል ደግሞ የሀሪያና ከተማ አስተዳደር የውጪ ጉዳይ ዋና ፀሐፊ ዮጀንደር ቻውድሀሪ ተፈራርመዋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱ በሁለቱ አካላት የኢንቨስትመንት አማራጮችን ከማስተዋወቅ አንፃር በጋራ ለመስራት እንደሆነ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በመዝጊያ ስነ-ስርዓቱ ላይ በኢትዮጵያ የሚገኙ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያሉ የስራ እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲሁም ቅድሚያ ስለሚሰጣቸው ሁኔታዎች ለሀሪያና ከተማ አስተዳደር እና በህንድ ለሚገኘው የቢዝነስ ማህበረሰብ በጋርመንትና ቴክስታይል፣ በፋርማሲዩቲካል እንዲሁም በአግሮ ኢንዱስትሪ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ገለፃ ተደርጓል፡፡