Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ በተገነቡ 67 ቤቶችና 43 አጥሮች ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጀሞ ወረዳ 1መንደር 3 በተለምዶ ሱቂ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በህገ ወጥ መንገድ በተገነቡ 67 ቤቶችና 43 አጥሮች ላይ እርምጃ መወሰዱን የክፍለ ከተማው አስተዳደር አስታውቋል ፡፡
 
በማስፋፊያ የደቡብ ምዕራብ የመዲናይቱ ዳርቻዎች የተከበበው የክፍለ ከተማው አስተዳደር የመሬት ወረራን እና ህገ ወጥ ግንባታን በመከላከል ረገድ ከአርሶ አደሮች፣ ከጸጥታ አካላትና ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት መደረጉ ተመላክቷል፡፡
 
ህገ ወጥ የመሬት ወረራን ለማቆም እና ህገወጥ ተግባራትን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ውጤታማ ሊባል ቢችልም አሁንም ድረስ በአሳቻ ጊዜ ተገንብተው የሚገኙ ቤቶችንና አጥሮችን በማፍረስ እርምጃ መውሰድ መቀጠሉን ነው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ያስታወቀው፡፡
 
በዛሬው ዕለትም በጀሞ ወረዳ 1መንደር 3 በተለምዶ ሱቂ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተደረገ የግብረ ኃይሉ እንቅስቃሴ 67 ቤቶችና 43 አጥሮች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገልጿል፡፡
ህገ ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከልም ነዋሪውን አይንና ጆሮ በማድረግ ጥቆማዎችን በመቀበል የቅድመ መከላከል ስራ ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መጠቆሙንም ከክፍለ ከተማው ኮሙኒኬሽን ያገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
የደንብ አስከባሪዎች እና የፀጥታ አካላትም በቅድመ መከላከል ተግባርም ይሁን ግንባታዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ በሚወሰድበት ወቅትም ተገቢውን ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ተመላክቷል።
 
በትላንትናው ዕለት በክፍለ ከተማው ወረዳ 9 ከለሊቱ 11ሰዓት ጀምሮ 150 ሰዎች የተሳተፉበት የመሬት ወረራ በፖሊስ፣በህዝቡና በአመራሩ ጥምረት ከሽፎ ግለሰቦቹ በህግ ጥላ ስር ሆነው ጉዳዩ ጥልቅ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑ ይታወቃል።
Exit mobile version