አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዲጂታል ፋውንዴሽን ፕሮጀክት የዓለም ባንክ ባስቀመጠው የአካባቢ እና ማህበራዊ ተፅዕኖዎች ቅነሳ መስፈርት መሰረት እየተተገበረ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
ሚኒስቴሩ የዓለም ባንክ በሚደግፈው የዲጂታል ፋውንዴሽን ፕሮጀክት የማህበራዊና አካባቢ ተፅዕኖ ቅነሳ አተገባበር ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው።
ምክክሩ ፕርጀክቱ በተሟላ ሁኔታ ሲተገበር የሚፈጠሩ የአካባቢ እና ማህበራዊ ተፅዕኖዎችን ለመቀነስ የሚያስችሉ መሳሪያዎች አስፈላጊነትና አጠቃቀም፣ በአፈፃፀም ወቅት የሚፈጠሩ ቅሬታዎች እና የቅሬታ የአፈታት ስርዓት ላይ በቂ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ መሆኑን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ባደረጉት ንግግር÷ መድረኩ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማን በተሻለ ሁኔታ ለማሳካትና የፕሮጀክቱን ትግበራና አፈፃፀም ለማሻሻል እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ የሚመራው የዲጂታል ፋውንዴሽን ፕሮጀክት ውስጥ የገንዘብ እና የትምህርት ሚኒስቴር፣ የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር እንዲሁም የኮሙኒኬሽን ባለስልጣን እና የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት መካተታቸው ተገልጿል።