Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ኩባንያ የተለያዩ የቅጣት ውሳኔዎችን አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ሚያዝያ 3፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየርሊግ ኩባንያ በ17ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ላይ በታዩ የስነ ምግባር ግድፈቶች ላይ የቅጣት ውሳኔ አሳልፏል፡፡

አዳማ ከተማ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር በነበረው የ17ኛ ሳምንት ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች የእለቱን ዳኛና የተጋጣሚ ቡድን አሰልጣኝን አፀያፊ ስደብ መሳደባቸውን ተከትሎ 50 ሺህ ብር እንዲከፍል መወሰኑን አስታውቋል።

ቀደም ብሎ በተካሄደውና ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ባደረጉት ጨዋታም የክለቡ ደጋፊዎች የተጋጣሚ ቡድን አመራሮችን ስለመሳደባቸው እና ቁርጥራጭ ወንበሮችን ወደሜዳ ስለመወርወራቸው እንዲሁም 42 ወንበሮች በደጋፊዎች የተቆረጡ፣ የተሰነጠቁ ወይም የተነቀሉ ስለመሆናቸው ሪፖርት መቅረቡን ኩባንያው ገልጿል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የክለቡ ደጋፊዎች ለፈፀሙት ጥፋትና ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ ክለቡ መቀጣቱና ደጋፊዎቹም ሊታረሙ አለመቻላቸውን ታሳቢ በማድረግ ክለቡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን ምዕራፍ 3 አንቀፅ 66 በተራ ቁጥር 4(ሀ) መሰረት 75 ሺህ ብር እንዲከፍል ተወስኗል።

ቅዱስ ጊዮርጊስም የክለቡ ደጋፊዎች ቁርጥራጭ ወንበሮችን ወደሜዳ ስለመወርወራቸው እንዲሁም 34 ወንበሮች የተቆረጡ፣ የተሰነጠቁ ወይም የተነቀሉ ስለመሆናቸው ሪፖርት ቀርቦ 25 ሺህ ብር እንዲከፍል መወሰኑን የኩባንያው መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version