አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ‘ኤች አር 6600’ እና ‘ኤስ.3199’ ረቂቅ ሕጎችን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ ተካሄዷል።
በዋይት ሃውስ ፊት ለፊት በተካሄደው ሰልፍ፥ ረቂቅ ሕጎቹ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን የሚጎዱ በመሆናቸው ሊጸድቁ አይገባም ሲሉ ሰልፈኞቹ መልዕክት ማስተላለፋቸውን የሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ የዋሺንግተን ዲሲ ግብረ ኃይል ገልጿል።
ሕጎቹ ለረጅም ጊዜ የቆየውን የኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነት የሚጎዳ እንደሆነና የሁለቱ አገራት ጥቅም የማያስጠብቅ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሰልፈኞቹ ‘ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎች ጎጂ በመሆናቸው ሊሰረዙ ይገባል ብለዋል።
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በተያያዘ ዜና ‘ኤች አር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ በካሊፎርኒያ ግዛት ሎስ አንጀለስ ከተማ ይካሄዳል።
በሰልፉ ላይ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን እንደሚሳተፉ ከሰልፉ አስተባባሪዎች የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
ሰልፎቹ በረቂቅ ሕጉና የሕጉ ተባባሪ አርቃቂ በሆኑት የካሊፎርኒያው የኮንግረስ አባል ብራድ ሼርማን ላይ ተቃውሟቸውን እንደሚያሰሙ ተገልጿል።
‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ‘ኤች አር 6600’ በአሜሪካ የኮንግረስ አባል ቶም ማሊኖውስኪ (ኒውጀርሲ) ዋና አርቃቂነት፣ በያንግ ኪም (ካሊፎርኒያ)፣ ግሪጎሪ ሚክስ (ኒው ዮርክ)፣ ዴቪድ ሲሲሊን (ሮድ አይላንድስ)፣ ብራድ ሼርማን(ካሊፎርኒያ) እና ማይክል ማካውል (ቴክሳስ) ደጋፊነት በኮንግረሱ የተዘጋጀ ረቂቅ ሕግ ነው።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!