አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በሁለተኛው የአፍሪካ ቴኳንዶ ሻምፒዮና ውድድር አሸናፊ ሆነች።
ለሁለት ቀናት በራስ ኃይሉ ስፖርት ትምህርትና ስልጠና ማዕከል ሲካሄድ የነበረው ሻምፒዮና ተጠናቋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቴኳንዶ ሻምፒዮና በሁለቱም ጾታዎች በ24 ወርቅ፣ በ23 ብርና በ33 ነሐስ በድምሩ 80 ሜዳሊያዎችን በማግኘትበበላይነት አጠናቃለች።
ሜዳሊያዎቹ የተገኙት በቴኳንዶ ትዕይንት፣ ፍልሚያ እና ‘ፖወር ቴስት’ በተሰኙ የውድድር አይነቶች ነው።
ሴኔጋል በአንድ ወርቅ ሁለተኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን÷ ሞዛምፒክ በ2 የብር ሜዳሊያ ሶስተኛ ወጥታለች።
በወንዶች በእምነት ሹሜና አቤነዘር መኮንን እንዲሁም በሴቶች ዳግም ኪሮስና ሀና አበባየሁ የሻምፒዮናው ኮከብ ተጫዋች ሽልማት አግኝተዋል።
በሻምፒዮናው ላይ ኢትዮጵያ፣ጋምቢያ፣ ሴኔጋል፣ ኡጋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ታንዛንያ ፣ ኮቲዲቯር፣ ሞዛምቢክ፣ ጂቡቲ፣ ብሩንዲና ዚምባብዌ መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።