አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሰብአዊ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ የኢትዮጵያ ቢሮ አስታወቀ።
የማስተባበሪያ ቢሮው ሃላፊ ሚሼል ሳድ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት÷ በኢትዮጵያ ብዙ ሰዎች ሰብአዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በጦርነትና በግጭት እንዲሁም በድርቅ ምክንያት ብዙ ሰዎች ለችግር መዳረጋቸውን አንስተዋል።
በመሆኑም የሰብዓዊ ቀውሱን ለማቃለል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን አክለዋል።
በተለይም ሁሉንም ጥረቶችን በአንድ ላይ በማሰባሰብ ምን ማገዝ እና ያለውን ፍላጎት እንዴት ማሟላት እንደሚቻል በጋራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ ቢሮው ከ 22 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ ከ ሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ መድቦ እየሰራ ነው።
በቀጣይ ካለው የተረጂዎች ብዛት አንጻር ለጋሾች ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
በርካታ ተረጂዎች ባሉባቸው በአፋር እና አማራ ክልሎች ባለፉት ሁለት ሳምንታት የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት ማደጉን ተናግረዋል።
በቅርቡም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አጋር የሆኑ ተቋማት ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ በየብስ እንዲገባ መፈቀዱም ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ስምንት አይነት የጭነት ቁሳቁሶች ወደ ትግራይ በአየር ሲጓጓዝ መቆየቱን አስታውሰው አሁን ደግሞ የየብስ ጉዞ መጀመሩ የእርዳታ ተደራሽነቱን ያሳድገዋል ብለዋል።
አሁንም ማስተባበሪያ ቢሮው በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!