Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በመዲናዋ በተደራጀ መንገድ የመሬት ወረራ ለመፈፀም ሲዘጋጁ ነበር የተባሉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 2፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተደራጀ መንገድ የመሬት ወረራ ለመፈፀም ሲዘጋጁ ነበር የተባሉ ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡
 
ግለሰቦቹ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ወረዳ 9 ቀጠና 3 ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ጀርባ ( አፓርታማ አካባቢ) በተደራጀ መንገድ በአካባቢ ጥበቃ ለአረንጓዴ ልማት በህጋዊ ካርታ በተሰጠው ስፍራ በተለያየ ግዜ በመግባትና ደን በመጨፍጨፍ በህገወጥ መንገድ መሬት ለመውረር ሲዘጋጁ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።
 
ዛሬ ማለዳ 12 ሰዓት ላይ በቁጥጥር ስር የዋሉት 97 የሚደርሱ ግለሰቦች ( 20 ሴቶችና 77 ወንዶች) ከቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12፣ ከአቃ ቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 እና 6 የመጡ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
 
በተያዙበት ወቅት በወረዳው የሚገኙ ወጣቶችን በማሳመን የተጠቀሰውን ለአረንጓዴ ልማት የተከለለ ቦታን በመቆጣጠርና በመንግስት አስተዳደር ላይ ጫና በመፍጠር ቦታውን በህገ ወጥ መንገድ በመውረር በቁጥጥራቸው ስር ለማዋል አቅደው እንደነበረ ከሰጡት ቃል ለማረጋገጥ ተችሏል።
 
በህገ ወጥ የመሬት ወረራው 150 የሚደርሱ ግለሰቦች እጃቸው ያለበት ሲሆን÷10 ግለሰቦች በማለዳ በተካሄደው ኦፕሬሽን ማምለጣቸው ተገልጿል፡፡
 
ጉዳዩ ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ውለው በፖሊስና በሚመለከታቸው አካላት ተጨማሪ የማጥራት ስራ እየተሰራ መሆኑን ከክፍለ ከተማው ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
Exit mobile version