አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተገኙ ውጤቶች ሳንዘናጋ በክልሉ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት መረባረብ አለብን ሲሉ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የክልሉ የመንግስት የሶስተኛ ሩብ ዓመት አፈፃፀም ግምገማ ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባደረጉት ንግግር፥ ባለፉት ሶስት ወራት በአሰራርና በዕቅድ ከመምራት አንፃር ተስፋ ሰጪ ሂደቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በተለይ የሰላም እጦት መንስኤዎችን ከመለየት፣ የህዝቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮች ከማጥራትና መፍትሔ ከማበጀት አኳያ መልካም ጅምሮች አሉ ብለዋል ።
ህብረተሰቡ ወቅታዊ የፀጥታ ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት በባለቤትነት እንዲሳተፍ በማድረግ፣ በዜግነት አገልግሎት፣ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ የተሻለ ስራ መከናወኑን አመላክተዋል።
ባለፉት ሶስት ወራት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት የአፈርና ውሃ ዕቀባ፣ የዕርከን ስራና ባለፈው ክረምት የተተከሉ ችግኞች እንክብካቤ መካሄዱንም ጠቅሰዋል።
የልማት፣ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማቃለል የሚያስችሉ ሂደቶች መለየታቸውን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ለብልፅግና ጉዞ ስኬት መሰረት መጣል መቻሉን ገልጸዋል።
በቀጣይ ሶስት ወራት በትኩረት የሚሰሩ ጉዳዮች መለየታቸውን በመጠቆም፥ የበልግ አዝመራ፣ የመኸር እርሻ ማሳና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት፣ የኬሚካል ማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦት ትኩረት እንደሚሰጣቸውም አስረድተዋል።
የ2015 በጀት ዓመት የክልሉ የልማት ዕቅድ ዝግጅት፣ አማራጭ የገቢ ምንጮችን ማስፋትና ገቢን አሟጦ መሰብሰብ፣ የጤና አገልግሎት ማሻሻልና የትምህርት ሴክተር ትኩረት የተሰጣቸው መሆናቸውን አውስተዋል።
የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት፣ የመሬት አስተዳደር፣ የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራር ማስወገድ ለነገ የማይባል አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑንም ነው የገለጹት።
ባለፉት ሶስት ወራት የአፈፃፀም ውስንነትና ክፍተት የታየባቸው የልማት ፕሮጄክቶች የግንባታ መዘግየት፣ የክልሉ ሰላምና ፀጥታን ማስፈንና ሸኔን ከማጥፋት አንፃር በቀጣይ ሰፊ ርብርብ የሚደረግባቸው አጀንዳችን ናቸው ብለዋል አቶ ሽመልስ።
“ግምገማው ችግሮቻችንን አንጥረን ያወጣንበት ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ለህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በየደረጃው ያለው አመራር ህብረተሰቡን በማሳተፍ ርብርብ እያደረገ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!