የሀገር ውስጥ ዜና

የኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ ሕጎችን የሚቃወሙ ሰላማዊ ሰልፎች በአሜሪካ ከተሞች ሊካሄዱ ነው

By Meseret Awoke

April 09, 2022

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የ ’ኤች አር 6600 እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎች የሚቃወሙ ሰላማዊ ሰልፎች በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲና ሎስ አንጀለስ ከተሞች ይካሄዳሉ።

ነገ በዋሺንግተን ዲሲ ዋይት ሃውስ ፊት ለፊት እንደሚካሄድ ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር የዋሺንግተን ዲሲ ግብረ ሃይል ሰብሳቢ አቶ ጣሰው መላከህይወት ገልጸዋል።

“ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን የሚጎዳ ነው” ፣ ”ሕጎቹ የኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነትን የሚጎዱ ናቸው” ፣ ”ማዕቀብ ይገላል” እና “ኤችአር 6600 እና ኤስ 3199 ይሰረዙ” የሚሉ መፈክሮች በሰልፈኞቹ እንደሚተላለፉ አመልክተዋል።

በሰልፉ ላይ ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ኤርትራውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

ዳያስፖራው ሕጎቹ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት በየአካባቢያቸው ለሚገኙ የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮች በማስረዳት እንዳይደግፉት የማድረግ ጥረቱን ማጠናከር እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።

በዳያስፖራው አደረጃጀት በኩል ሕጎቹ ድምጽ እንዳይሰጥባቸው ተሰሚነት ያላቸውን የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮች የማነጋጋር ስራ እየተከናወነ እንደሆነ አስረድተዋል።

መንግስት ከአሜሪካ መንግስት ጋር በሚኖረው ግንኙነት ረቂቅ ሕጎቹ እንዳይጸድቁ የሚያደርገው የዲፕሎማሲ ጥረትና በቅርቡ የወሰዳቸው እርምጃዎች የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ወሳኝ እንደሆነ ነው አቶ ጣሰው የገለጹት።

ዳያስፖራው በአንድነት በመቆም ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥሉት ሕጎች እንዳይጸድቁ አስፈላጊውን ጥረት እንዲያደረጉ አቶ ጣሰው ጥሪ አቅርበዋል።

በተያያዘ ዜና ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ከነገ በስቲያ በካሊፎርኒያ ግዛት ሎስ አንጀለስ ከተማ ይካሄዳል።

በሰልፉ ላይ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን እንደሚሳተፉ ኢዜአ ከሰልፉ አስተባባሪዎች ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ሰልፎቹ በረቂቅ ሕጉና የሕጉ ተባባሪ አርቃቂ በሆኑት የካሊፎርኒያው የኮንግረስ አባል ብራድ ሼርማን ላይ ተቃውሞ እንደሚያሰሙ ተነግሯል። ትውልደ ኢትዮጵያውያኑና ኤርትራውያኑ በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም በሚካሄደው የኮንግረስ ምርጫ ለሚወዳደሩት ብራድ ሼርማን ድምጽ እንደማይሰጡ ግልጽ መልዕክት ያስተላልፋሉ።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!