Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኬር ኢትዮጵያ ለደቡብ ወሎ ዞን የ10 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ጀኔሬተሮችና የውኃ ፓምፖችን ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣መጋቢት 30፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኬር ኢትዮጵያ በደቡብ ወሎ ዞን በጦርነቱ ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸው የውኃ ተቋማት አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያግዝ ከ10 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ጀኔሬተሮችና የውኃ ፓምፖችን ድጋፍ አደረገ፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት የኬር ኢትዮጵያ የምህንድስና ባለሙያ ወይዘሮ አዝመራ ስማቸው÷ድጋፉ የውሃ ተቋሞችን መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት አጋዥ ሊሆኑ የሚችሉ ከ10 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ 10 ጀኔተሮችና 4 የውኃ ፓምፖችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት ወይዘሮ አዝመራ፥ ሙያዊ ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ በጋራ እንደሚሰሩ አብራርተዋል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት የደቡብ ወሎ ዞን ውኃና ኢነርጅ መምሪያ የውኃ ጥራት ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ንጉስ ተፈራ በበኩላቸው፥ የውሃ ተቋሞችን መልሶ በማደስና በመጠገን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ጥረት ቢደረግም ተቋሞቹ ከደረሰባቸው ውድመት አንፃር ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ባለመቻሉ ህብረተሰቡ የንጹህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ እንዳልሆነ አብራርተዋል፡፡
በዚህም ከ342 ሺህ በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የንፁህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ጠቁመው፥ ኬር ኢትዮጵያ አሁን ያደረገው ድጋፍ ከ40 ሺህ በላይ የኀብረተስብ ክፍል የንፁህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ነው ብለዋል፡፡
የተደረገው ድጋፍ በጦርነቱ ክፉኛ ለተጎዱ አካባቢዎች ማለትም ለአምባሰል፣ ወረባቦ፣ ቃሉ፣ ደላንታ፣ ለገሂዳ፣ ወረኢሉና ጃማ ወረዳዎች እንደሚሰጥ መጠቆማቸውን ከደቡብ ወሎ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የሽብር ቡድኑ ህወሃት በዞኑ ግምታቸው ከ1 ነጥብ 15 ቢሊየን ብር በላይ የሆኑ 672 የገጠርና 56 የከተማ የውኃ ተቋሞች ላይ ጉዳት ማድረሱን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version