Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከባድ የክረምት ዝናብ በሚፈጥረው “ላሊና” ምክንያት የሚከሰትን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል  ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ አቶ ደመቀ መኮንን አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከባድ የክረምት ዝናብ በሚፈጥረው “ላሊና” ምክንያት የሚከሰትን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳሰቡ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሰብሳቢነት የሚመሩት የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ቤት ስብሳባ ዛሬ ተካሂዷል፡፡

ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የሚመለከታቸው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የበላይ ኃላፊዎች የተካተቱበት ምክር ቤት የጎርፍ አደጋን በመከላከል፣ እንቦጭን በማስወገድና በአረንጓዴ አሻራ ዙሪያ ተወያይቶ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ ካሉት 12ቱ ዋና ዋና ተፋሰሶች ከአዋሽ ተፋሰስ ውጭ በሌሎች አካባቢዎች በቂ የተፋሰስ ሥራ እንዳልተከናወነ ተገልጿል፡፡

የስምጥ ሸለቆ ሀይቆችና የአባይ ተፋሰስ ላይ የሚከናወኑ የተፋሰስ ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ ሲሆኑ÷ የኦሞ ጊቤ፣ ዋቢ ሸበሌና ገናሌ ዳዋ ተፋሰሶች ግን በጅምር ላይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የተፋሰስ ሥራዎች ወቅታቸውን ጠብቀው ሙሉ በሙሉ ካልተጠናቀቁ በቀሪዎቹ ብቻ ሳይሆን የተሰሩትንም ጭምር የሚያበላሹ በመሆናቸው በቂ ትኩረት እንዲደረግም  ነው ተሳታፊዎቹ የጠየቁት፡፡

በደቡብ ክልል የዳሰነች ማህበረሰብ በጊቤ ሰው ሰራሽ ሀይቅ እንዲሁም በአፋር ክልል በአዋሽ ወንዝ ምክንያት ጉዳት እንዳይደርስ  ፈጣን ምላሽ እንደሚያስፈልገው መጠቆሙን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል፡፡

የባሮ ወንዝ ለጋምቤላ ከተማ ስጋት እንደሆነ  መቀጠሉንና ከጊቤ ሦስት ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሚለቀቅ ከፍተኛ ውሃም ትምህርት ቤቶች ጤና ተቋማትን ማውደሙን በዚህም በአንድ ዓመት ብቻ ከ117 ሺህ በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸውንም ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ሰው ሰራሽ ግድብ አካባቢ የተከሰተ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ከ110 ሺህ በላይ ዜጎችን ተረጂ እንዲሆኑ ማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡

የጣና በለስ ፕሮጀክት ከ15 ሺህ በላይ አሳ አስጋሪዎችን ጨምሮ በሚሊየን የሚቆጠሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን  ተጎጂ እያደረጋቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version