አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን በጥራት እና በወቅቱ እንዲያቀርብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተጠየቀ፡፡
ቋሚ ኮሚቴ የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን የ6 ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ሪፖርት የገመገመ ሲሆን÷ በተቋሙ ውስጥ የኦዲት አገልግሎትም ሆነ የድጋፍ አገልግሎት ሥራዎች ወጪ ቆጣቢ ለማድረግ የሚያስችል ወረቀት- አልባ ስርዓት በተግባር ላይ መዋሉ የሚበረታታ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በቀጣይ እያሻሻለ ለመሄድ ያሳየውን ቁርጠኝነት ቋሚ ኮሚቴው በአድናቆት የተመለከተ ቢሆንም÷ ሪፖርቶችን ጠምሮ ጥራት ባለው መንገድ፣ ወቅቱን ጠብቆና አደራጅቶ ለሚመለከተው አካል መላክ እንዳለበት አሳስቧል፡፡
ተቋሙ በ6 ወር ውስጥ ጎልተው የሚታዩ ሥራዎችን ማከናወኑም የተገለጸ ሲሆን ÷ ከኦዲት ግኝቶች ባሻገር ተቋማት የራሳቸውን ተልዕኮ፣ ራዕይ እና ዓላማ ከማሳካት በዘለለ፣ ሕግን እና ስርዓትን ተከትለው እንዲሠሩ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡
ተቋሙ ከቋሚ ኮሚቴው ጋር የፈጠረውን ጥሩ መናበብ አጠናክሮ እንዲቀጥል የጠየቁት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ክርስቲያን ታደለ÷በኦዲት አሠራር የሒሳብ ጉድለት የተገኘባቸውን ተቋማት በይፋዊ የሕዝብ መድረክ ስለ ግኝቱ ዝርዝር ማብራሪያዎችን በመስጠት እና ተጨማሪ የግልጸኝነት ጥያቄዎችን በማንሳት ተቋሙ የሚያደርገውን ጥልቀት ያለውን ተሳትፎ በኮሚቴው ስም አመስግነዋል፡፡
ሪፖርቱ በቀጣይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊመጥን በሚችል ደረጃ በጥራት እና በወቅቱ ተደራጅቶ መቅረብ አለበት ማለታቸውንም ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
“እንድናስተካክላቸው በኮሚቴው የተሰጡ ግብዓቶችን ተጠቅመን ሪፖርቱን በወቅቱና ጥራቱን በጠበቀ መንገድ እንዲቀርብ በትኩረት እንሠራለን” ያሉት ደግሞ የመሥሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!