Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሸበሌ ዞን የመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በሶማሌ ክልል በሸበሌ ዞን አዲሌ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ ፈርቡሮ እና ኮሌዳ የመጠለያ ጣቢያዎች በድርቁ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ተመልክቷል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ቤተልሔም ላቀው÷ የክልሉ አመራር ድርቁ ያስከተለውን ጉዳት ለመከላከል በርካታ ተግባራትን ያከናወነ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

የድርቁን አሳሳቢነት እና እያስከተለ ያለውን ጉዳት የሚዲያ ሽፋን በመስጠት የኢትዮጵያ ህዝብ በሚገባ አውቆት ተገቢውን እርዳታ እንዲሰጥ ከማድረግ አንፃር የክልሉ መንግስት በትኩረት መስራት እንዳለበትም ነው ምክትል ሰብሳቢዋ ያሳሰቡት።

በሸበሌ ዞን በሁለቱም የመጠለያ ጣቢያዎች 3 ሺህ 960 አባወራዎች በድርቅ የተፈናቀሉ ሲሆኑ÷ የምግብ፣ ውሃ እና የህክምና አገልግሎት በመንግስት እና በረድኤት ድርጅቶች አማካኝነት ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም አቅርቦቱ ተመጣጣኝ አለመሆኑን የቋሚ ኮሚቴው አባላት ተናግረዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ÷ ዜጎች በዚህ ደረጃ ተጎሳቁለውና ተንገላትተው ማየታቸው እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡ ይህን ችግር በተባበረ ክንድ ለመቀልበስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በመተጋገዝ የዜጎችን ህይወት መታደግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ÷ የድርቁ አስከፊነት ለአርባ ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ በመሆኑ ከ1 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ የአርብቶ አደሩ እንስሳት መሞታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዘጠኝ ዞኖች ዝናብ ባለመዝነቡ የተከሰተው ድርቅ የተለየ በመሆኑ÷ የክልሉ መንግስት ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት 15 ሚሊየን ብር በመመደብ በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የውሃ፣ ምግብና የመድሃኒት አቅርቦት አድርጓል ብሏል፡፡

በቀጣይም ዝናብ ካልዘነበ የድርቁ ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ የፌዴራል መንግስት ተጨማሪ በጀት መፍቀድ እንዳለበት አንስተዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሀመድ የሱፍ÷ በክልሉ በበርካታ ወረዳዎች ዝናብ ባለመዝነቡ የአርብቶ አደሩ የኢኮኖሚ መሰረት የሆነው እንስሳት ስለሞቱባቸው በመጠለያ ጣቢያዎች ህይወታቸውን እንዲመሩ መገደዳቸውን ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል፡፡

በድርቁ የተጎዱ ዜጎች በበኩላቸው÷ የሚደረገው ድጋፍ በቂ እንዳልሆነ እና በሚደርሱ እርዳታዎችም ፍትሃዊ ያልሆኑ አሰራሮች እየተስተዋሉ በመሆናቸው የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲሰጥበት መጠየቃቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version