አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 30 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልልን ከአማራ ክልል ጋር በመንገድ መሰረተ ልማት የሚያስተሳስሩት የሙከጡሪ-ኮከብ መስክ እና ኮከብ መስክ-ዓለም ከተማ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በመስክ የስራ ቅኝት ተጎበኙ።
ለመንገዶቹ የግንባታ ስራ አመቺነት ሲባል በሁለት ኮንትራት ተከፍሎ እየተሰራ ሲሆን÷ ኮንትራት አንድ የሙከጡሪ-ኮከብ መስክ እና ኮንትራንት ሁለት ኮከብ መስክ-ዓለም ከተማን ያካልላል ተብሏል፡፡
ሙከጡሪ-ኮከብ መስክ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን በያዝነው በጅት ዓመት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑም በመስክ ቅኝቱ ተመላክቷል።
የፕሮጀክቱ አፈፃፀም 80 በመቶ የደረሰ ሲሆን÷ 59 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለው እና 40 ኪሎ ሜትር የሚሆን የአስፋልት ንጣፍ ስራው እንደተጠናቀቀ ተገልጿል፡፡
ቀሪና የማጠቃለያ ስራዎችን ለመፈጸም እየተሰራ ሲሆን÷ በዚህም ደህንነትን የሚጠቁሙ የትራፊክ ምልክቶች እየተመረቱ መሆናቸውን ግንባታውን የሚያከናውነው ቻይና ሪልዌይ ቁጥር ሶስት ኢንጂነሪንግ ግሩፕ አስታውቋል፡፡
መንገዱን ለመገንባት የሚያስፈልገው ወጪ 768 ሚሊየን 6 መቶ 22 ሺህ ብር ሲሆን÷ ወጪዉም በመንግስት መሸፈኑ ተመላክቷል፡፡
የመንገድ ግንባታው በገጠር 10 ሜትር፣ በቀበሌ 12 ሜትር በወረዳ ደግሞ 21 ሜትር ስፋት ያለው ነው ተብሏል፡፡
በተመሳሳይ ኮከብ መስክ-አለም ከተማ የመንገድ ፕሮጀክት ስራ 47 ኪሎ ሜት ርዝማኔ እንዳለው ታውቋል፡፡
መንገዱን እየገነባ ያለው ቻይና እስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሊሚትድ÷ በእስካሁኑ የሥራ እንቅስቃሴ የዲዛይን ስራ፣ ቅየሳ፣ የአፈር ቆረጣ፣ ሙሌት እና የጠረጋ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታወቋል፡፡
105 ሜትር ርዝመት ያለዉ የጀማ ወንዝ ድልድይ የፕሮጀክቱ የግንባታ አካል ሲሆን÷ 4 ድልድዮችን 126 የከልቨርቶች ስራን በማካተት ስራው እየተከናወነ መሆኑን ከመንገዶች ባለስልጣን አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ለፕሮጀክቱ ወጪ 1 ቢሊየን 695 ሚሊየን 688 ብር የተመደበ ሲሆን÷ በመንግስት የሚሸፈን መሆኑ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!