አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 30 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘርፉ የካበተ ልምድ ያላቸው የቤልጂየም ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የፋርማሲዩቲካል ዘርፍ እንዲሳተፉ ለማድረግ የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በቤልጂየም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ አካላት የተሳተፉበት የኢንቨስትመንት ፎረም አካሂዷል፡፡ በዚሁ ውይይት ላይ በቤልጂየም የሚገኙ ኢንቨስተሮች በፋርማሲዩቲካል የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።
በውይይቱ በቤልጂየም የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሂሩት ዘመነን ጨምሮ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ሳንዶካን ደበበ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ እንዲሁም የጤና ሚኒስቴር እና የምግብ መድኀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
ኢትዮጵያ በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ያላትን አጠቃላይ እንቅስቃሴ፣ በዘርፉ ሊኖር የሚገባ እድገትን እንዲሁም ኢትዮጵያ በዘርፉ ለሚሰማሩ ኢንቨስተሮች ያስቀመጠችውን ፖሊሲ አስመልክቶ የጤና ሚኒስቴር ተወካይ ዶክተር ፋሲካ መከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ÷ኮርፖሬሽኑ 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመላው ሀገሪቱ ገንብቶ እና አልምቶ እያስተዳደረ እና ለኢትዮጵያ የውጪ ምንዛሬ ገቢ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ለሚሰማሩ አምራች ኩባንያዎች በተለየ መልኩ ለዘርፉ ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘውን የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክን ከሌሎች ማበረታቻዎች ጋር ለባለሀብቶች መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡
ውይይቱ በቤልጂየም የሚገኙ ባለሀብቶች በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎችን በኢትዮጵያ ባሉ ኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፉ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ከኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላታክል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!