Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ ከሁሉም አገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ጽኑ ፍላጎት አላት – ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 29 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከሁሉም አገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ጽኑ ፍላጎት እንዳላት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የፍትህ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህ ወቅትም መንግሥት ለሰብዓዊ ድጋፍ ሲባል የወሰነው የግጭት ማቆም እርምጃ ለሰብዓዊ ጉዳዮችና ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋገጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከኮቪድ-19 ወረረሽኝ በኋላ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በለኮሰው ጦርነት፥ በተወሰኑ አካባቢዎች በተከሰተ ድርቅና በሌሎች ውጫዊ ጫናዎች ፈርጀ ብዙ ፈተናዎች ተጋርጠውበታል ብለዋል።

ይሁንና መንግሥት የአገሪቷን ሉዓላዊነትና የሕዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፥ በችግር ላይ የወደቁ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ላደረጉት የሰብዓዊ ድጋፍ አመስግነዋል።

የዜጎች ሕይወት ጉዳይ በመሆኑ መንግሥት በትግራይም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

በሌላ በኩል ለአገሪቷ ዘላቂ ሰላም ብሔራዊ ምክክር ለማካሄድ እየሰራ መሆኑን አብራርተው፥ ጦርነቱ በተካሄደበት ሥፍራዎች የተፈፀሙ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን አጣርቶ የወንጀል ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በዚህም ቀደም ብሎ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ ባካሄዱት ምርመራ መሰረት በሁሉም ወገን ያሉ የመብት ጥሰት የፈፀሙ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ኮሚቴ አቋቁሞ ሲሰራ መቆየቱ አስታውሰዋል።

በአንዳንድ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በኩል ጥረቷን ያለማክበርና ዕውቅና የመንሳት አዝማሚያዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

በቅርቡ መንግሥት የወሰነው የሰብዓዊ ግጭት ማቆም ውሳኔም መንግሥት ላልተገደበ ሰብዓዊ እርዳታና ሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠበት መሆኑን ተናግረዋል።

ሰሞኑን በአምነስቲ ኢንተርናሽናልና በሂዩማን ራይትስ ዎች የወጣው ሪፖርት የአንድ ወገን የፖለቲካ ፍላጎት የተንፀባረቀበትና ነባራዊውን ዕውነታ የማያሳይ በመሆኑ መንግሥት እንደማይቀበለውና ቅሬታውን እንደገለፀ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ነፃና ገለልተኛ ተቋም እንደሆነ ገልፀው፤ ኮሚሽኑ የሚያወጣቸውን ተጨባጭ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርቶችን ተዓማኒነት በመካድ የሚገልጹ አካላትን ኮንነዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version