አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ በኢትዮጵያና በአሜሪካ መንግስታት የልማት ትብብር ሥራዎች ላይ መምከራቸውን አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ አምባሳደር ጃኮብሰን እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ሃላፊ ሼን ጆንስ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸው ወቅትም መንግስት ግጭት ለማቆም በወሰነው የተኩስ አቁም እና በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች እየተሰራጨ ባለው ሰብአዊ ድጋፍ ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።
በዚህ ወቅትም የዕርዳታ አቅርቦቱ በተገቢው ሁኔታ እየደረሰ መሆኑን መገምገማቸውንም አሜሪካውያኑ አድንቀዋል፡፡
ከአሜሪካ በኩል አሁን ላይ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦቱ ወደ ትግራይ ክልል እየደረሰ ያለበት ሁኔታ አበረታች መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ በቀጣይ ከትግራይ በኩል የዕርዳታ አቅርቦቱ እንዳይስተጓጎል የበኩላቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ÷መንግስት በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ክልሎች መልሶ ለማቋቋም እና ድጋፍ ለማድረስ ዕቅድ ነድፎ በሠራቸው ሥራዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም በቀጣይ ኢትዮጵያ ከገባችበት የሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የመሠረተ-ልማት ውድመት ቀውስ በሚገባ ለማገገም የልማት አጋር እና ድጋፍ እንደሚያሻት አመላክተዋል።
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት በኢትዮጵያ ሃላፊ በበኩላቸው ÷ በዚህ ዓመት በድርቅ ለተጠቁ የቀጠናው አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ አዲስ መርሃ-ግብር ቀርጸን እየተንቀሳቀስን ነው ብለዋል፡፡
መርሃ-ግብሩም በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ፣ በኬንያ እና በሶማሊያ ይፋ እንደሚሆን ነው የገለጹት፡፡
በቀጣይ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት እና የትብብር ሥራዎች አጠናክሮ ለማስቀጠል ሁለቱም ወገኖች ቁርጠኛ እንደሆኑ ማመላከታቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡