አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የሚዘጋጀው አዲስ ወግ “የኑሮ ውድነት መንስኤዎቹ እና የመፍትሔ ርምጃዎች” በሚል ርዕስ ተካሂዷል፡፡
የውይይት መድረኩ በፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዲኤታ በዶክተር ነመራ ገበየሁ ፣ በብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አቶ መለሰ ምናለ እና በኢትዮጵያ ህብረትሥራ ኮሚሽን የኅብረት ስራ ግብይት ዳይሬክተር ይርጋለም እንየው ሀሳብ አቅራቢነት እና በሮዛ መኮንን አመቻችነት መካሄዱን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አቶ መለሰ ምናለ “የኑሮ ውድነት /የገንዘብ ግሽበት በዜጎች የመግዛት አቅም መቀነስ የሚገለጽ መሆኑን በዚህ ወቅት ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም በፍላጎት እና አቅርቦት አለመመጣጠን፣ በምርት ስርጭት እና ግብይት ጉድለት፣ የበጀት አስተዳደር ጉድለት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ሁኔታዎች የኑሮ ውድነት መንስኤዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት ርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል ያሉት አማካሪው፥ የበጋ መስኖ ስንዴን ማምረት አንዱ መሆኑን በመጥቀስ ውጤቱን ለማየት መታገስ ያስፈልጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን የኅብረት ስራ ግብይት ዳይሬክተር ይርጋለም እንየው በበኩላቸው÷በአገራችን የግብይት ሰንሰለት የሚስተዋለው ርዝማኔ መሻሻል እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡
ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ሥራዎች እየተከወኑ እና የሕብረት ሥራ ማህበራትና በርካታ የሸማቾች ማህበራት ቢኖሩም እሴት የማይጨምሩ ሕገወጥ የግብይት ተዋናዮች መኖራቸው ተገቢው የዋጋ ተመን እንዳይኖር አድርጓል ነው ያሉት።
ምርታማነትን ማሳደግ፣ የአቅርቦት ክፍተትን መሙላት፣ የአምራችና የኢንደስትሪ ትስስርን ማጠናከር፣ የህብረት ሥራ ማኅበራትን የአሠራር ማዘመን እና ሕገ ወጥ የግብይት ተዋናዮችን መቆጣጠር ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ነመራ÷”በበቂ ሁኔታ የምግብ ፍጆታዎችን ለማምረት ያለመቻል ከውጪ ማስገባትን አስገዳጅ ያደርገዋል፤ይህም የውጪ ምንዛሬ አጠቃቀምና የዋጋ መረጋጋት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያመጣል ብለዋል፡፡
የኢንዱስትሪ የማምረት አቅም ከፍጆታ ጋር ለመጣጣም ብዙ ይቀረዋል ያሉት ዶክተር ነመራ÷መንግሥት ይህን ለመደጎም ምርቶችን ከውጪ ማስገባቱም የውጪ ምንዛሬን እንደሚጎዳ አስረድተዋል፡፡
የግብርና ምርቶችን ወይም የምግብ ፍጆታ ሸቀጦችን በብዙ እጥፍ ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመው÷የበጋ መስኖ ከስንዴ ባሻገር አትክልትና ጥራጥሬን ማምረት አስችሏል፤ በጥቂቱ ተጀምሮ ብዙ ውጤት ቢያስገኝም ገና ሰፊ ሥራ እንደሚጠበቅ አብራርተዋል፡፡
ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አቶ አሸናፊ ማሙዬ እንደ ዘይት ያሉ መሠረታዊ ፍጆታዎች በልማት ድርጅቶች በቀጥታ በልዩ ሁኔታ ተገዝተው እንዲቀርቡ፥ መንግሥት 27 ቢሊየን ብር ቀረጥ አስቀርቶ በቀጥታ ምርቶች ከውጪ እንዲገቡና ፋብሪካዎች እንዲጠናከሩ የሚያስች አሰራር መዘርጋቱን ጠቁመዋል፡፡
ምርቶች በቀጥታ ከአምራቾች ተገዝተው ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባወጣው ኮታ መሠረት ለሸማቾች እንዲቀርቡ ለማድረግ ሥራዎች ያለ ትርፍ ወጪን ብቻ በመቻል እየተከወኑ እንደሚገኙም የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ አቻ ደምሴ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!