Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ተሸከርካሪዎች የነዳጅ ድጎማ ማድረግ በሚያስችል ረቂቅ መመሪያ ላይ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 28 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመዲናዋ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ተሸከርካሪዎች የነዳጅ ድጎማ ማድረግ በሚያስችል ረቂቅ መመሪያ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
የድጎማ ስርዓቱ በአግባቡ ስራ ላይ መዋሉ ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የተሻለ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ያስችላል ተብሏል፡፡
በድጎማ ስርዓቱ ጂ ፒ ኤስ እንዲገጠም መደረጉም የትራንስፖርት ስምሪቱን በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር ቁጥጥሩን ለማሳለጥ ዕድል ይፈጥራል የተባለ ሲሆን÷ ድጎማው ከሀምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ አፈፃፀም ረቂቅ መመሪያ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
የነዳጅ ድጎማው ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ህብረተሰብ አገልግሎት የሚሰጡ በታሪፍ እና በስምሪት ቁጥጥር ላይ የተመሠረተ መለስተኛ፣ መካከለኛ የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ተሽከርካሪዎችን የሚመለከት ይሆናል ነው የተባለው፡፡
በዚህም መሰረት በመዲናዋ የህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሠጡ የመንግሥትና የግል አውቶቡሶች፣ የህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሠጡ ኮድ 1 እና ኮድ 3 ሚኒባስ (አዲስ አበባ ውስጥ የተመዘገቡ) ተሽከርካሪዎችን ያካትታል፡፡
ሆኖም ግን በመንግሥት መስሪያ ቤቶች፣ በግል እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሠራተኛ አገልግሎት እንዲሁም በግል ትምህርት ቤቶች የተማሪ አገልግሎት የሚሠጡ በዚህ የታለመ የድጎማ አሰራር አይካተቱም ተብሏል፡፡
በትራንስፖርት ቢሮ የህዝብ ጭነት ስምሪትና ድልድል ኦፕሬተር ፈቃድ ዳይሬክተር አቶ አልዓዛር ይርዳው ÷ ረቂቅ መመሪያው በአሁኑ ጊዜ እያደገ የመጣውን የነዳጅ ዋጋ ድጎማን በሂደት በማስቀረት ወደቀደመው የዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ አስተዳደር ሥርዓት እንዲመለስ ያስችላል ብለዋል፡፡
የነዳጅ ዋጋ ድጎማው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የጐላ ተፅዕኖ በማያስከትል አግባብ ለመተግበር የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት እንደሆነም አቶ አልዓዛር አስረድተዋል፡፡
በድጎማ ስርዓቱ የተመዘገቡ ተሽከርካሪዎች እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ጂ ፒ ኤስ መግጠም አስገዳጅ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ገልጸው እስከ ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም የተሽከርካሪዎች መረጃ ወደዳታ ቤዝ የማስገባት ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡
በመሆኑም በመዲናዋ በህዝብ ትራንስፖርት የተሰማሩ ተሽከርካሪዎችን የሚመለከቱ አጠቃላይ መረጃዎች በአስር ቀናት ተደራጅተው ለቢሮው እንዲላኩ አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version