የሀገር ውስጥ ዜና

በደቡብ ክልል ከደንብና መመሪያ ውጪ የተከፈለ ከ343 ሚሊየን ብር በላይ በሂሳብ ምርመራ ተገኘ

By Meseret Awoke

April 05, 2022

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 27 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል በተለያዩ ተቋማት ከደንብና መመሪያ ውጪ የተከፈለ ከ343 ሚሊየን ብር በላይ በሂሳብ ምርመራ መገኘቱ ተገለጸ።

የደቡብ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ምህረቱ አሰፋ እንደተናገሩት ÷ በክልሉ የመንግስት ሐብትና ንብረት የሚመሩባቸው ደንቦችንና መመሪያዎችን በአግባቡ መተግበር ላይ ክፍተት ተስተውሏል።

በክልሉ የተለያዩ መንግስታዊ መዋቅሮች ለሌብነትና ለብልሹ አሰራር የተጋለጡ መሆናቸውን ገልጸው ÷ ችግሩን በመፍታት ሐብቱን ለሚፈለገው ልማት ለማዋል አመራሩ መስራት አለበት ብለዋል።

በክልሉ ከ2013 ጀምሮ በተለያዩ ተቋማት በተደረጉ የሂሳብ ምርመራዎች ከደንብና መመሪያ ውጪ የተከፈለ ከ343 ሚሊየን ብር በላይ መገኘቱን ገልጸው፥ ክፍተቱ ከታየባቸው መካከል የግንባታ ዕቃዎች ግዥ፣ የውሎ አበል አከፋፈልና ጨረታ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ያለአግባብ ከተከፈለው ገንዘብ ውስጥ 141 ሚሊየን ብር ወደ መንግስት ካዝና እንዲመለስ መደረጉንም ተናግረዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ አቶ ምናሴ ዘውዴ በበኩላቸው÷ የመንግስትና ህዝብ ሐብት ለልማት ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በግማሽ የበጀት ዓመቱ ውስጥ በዞኑ ተቋማት ላይ በተደረገ የኦዲት ግኝት ከደንብና መመሪያ ውጪ ሊባክን የነበረ ከ15 ሚሊየን ብር በላይ ማስመለስ መቻሉን ጠቅሰዋል።

ከመመሪያ ውጪ በመስራት እጃቸው ያለበትን አካላት ለህግ የማቅረብ ስራ መጀመሩንም የኢዜአ ዘገባ ይጠቁማል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ፋይናንስ መምሪያ የተቋሙን የስድስት ወራት አፈፃፀም ከባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!