Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአዳማ – አዋሽ – መኢሶ 60 ኪ.ሜ. መንገድ ከባድ ጥገና ተጀመረ

አዲሰ አበባ፣መጋቢት 27፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮ-ጅቡቲ የትራንስፖርት ኮሪደር አካል የሆነው የአዳማ – አዋሽ – መኢሶ 60 ኪ.ሜትር መንገድ ከባድ ጥገና ተጀመረ።

መንገዱ ካለው ዘርፈ-ብዙ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፋይዳ አንፃር የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ከባድ ጥገና ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ ፍሰት በበቂ ሁኔታ ለማስተናገድ እና የገቢና ወጪ ንግዱን ለማቀላጠፍ እንዲቻልም ከፍተኛ የጥገና ስራው መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታውቋል።

በዚህም መሰረት የመንገድ ፕሮጀክቱ ግንባታ አካል የሆነው የአዳማ- ኪ.ሜ 60 ምዕራፍ-1 መንገድ፣ ለጥገናው የሚያስፈልጉ የጠጠር ማምረት ስራ እና ሌሎች ለግንባታው የሚረዱ የተለያዩ የቅድመ-ግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተመላክቷል።

እንዲሁም በፕሮጅክቱ ክልል ውስጥ የአስፋልት ፓቺንግ ሥራ እየተከናወነ ሲሆን ጥገናው የትራፊክ ፍሰቱን በማያስተጓጉል መልኩ በፍጥነት ለማከናወን እንዲቻል ተሽከርካሪዎች በተለዋጭ መንገድ እንዲጠቀሙ ተደርጓል።

ለከባድ ጥገናው የሚውለው ከ816 ሚሊዮን ብር በላይ ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን እንደሆነም ተገልጿል።

የመንገድ ጥገና ፕሮጀክቱ የአዳማ እና ቦሰት ወረዳዎችን እንዲሁም ዳቤ ሶሎቄ እና ወለንጪቲ ቀበሌዎችን የሚያገናኝ ነው።

የዚሁ መንገድ ቀጣይ ክፍል የሆነው ከኪ.ሜ 60 እስከ አዋሽ ያለው መንገድ ከኢትዮጵያ መንግስት በተመደበ 1.3 ቢሊዮን ብር ወጪ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጥገናው እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የቁጥጥር እና የማማከር ሥራውን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ስራዎች ኮርፖሬሽን እየሰራ አንደሚገኝም ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version