Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኅብረቱ አገራዊ ምክክሩ የታለመለትን ግብ ያሳካ ዘንድ የሲቪል ማህበረሰቡ ኃላፊነቱን ለመወጣት መዘጋጀቱን አስታወቀ

አዲሰ አበባ፣መጋቢት 26፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አገራዊ ምክክሩ የታለመለትን ግብ ያሳካ ዘንድ የሲቪል ማህበረሰቡ ሀገራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት አስታወቀ፡፡
 
የኅብረቱ ዳይሬክተር አቶ መስኡድ ገበየሁ እንደገለፁት÷በተለይም የህግ ፣የሰላምና የሰብአዊ መብቶች እና ሌሎች አንኳር ጉዳዮች ትኩረት እንዲሰጣቸዉ ዝግጅት እየተደረገ ነው ፡፡
 
መሰል የሲቪል ማህበራት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዓላማዎች እውን መሆን አዎንታዊ ሚና ሲጫዎቱ መቆየታቸውን እና በቀጣይም የምክክሩ ሂደት ይሰምር ዘንድ ሀሳብ ከማዋጣት ጀምሮ ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አመላክተዋል፡፡
 
የምክክሩ ሂደት ተዓማኒ ይሆን ዘንድ የአካታችነት ጉዳይ ልዩ ትኩረት ይሰጣዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፥በዚህ ሂደት ሲቪል ማህበራት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አብራረተዋል ፡፡
 
የመብቶችና ዴሞክራሲ እድገት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር በፍቃዱ ኃይሉ በበኩላቸው÷በእስከ አሁኑ ቅድመ ዝግጅት የታዩ ክፍተቶች እንዳይደገሙ እና በቀጣይም ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን እንጥራለን ብለዋል ፡፡
 
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የሲቪል ማህበራት የስራ ኃላፊዎቹ÷ማህበራቱ የሂደቱን አካታችነትና አሳታፊነት የመከታተል እንዲሁም እክል ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁኔታዎች በሚኖሩ ወቅት እርምት እንዲወሰድባቸዉ እንደሚሰሩም ሀሳባቸዉን አካፍለዋል፡፡
 
የተለያዩ የሲቪል ማህበራት ከአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ጋር ጠንካራ ስራዎችን በጋራ ለመስራት ከፍ ያለ መነሳሳት እንዳላቸውም የስራ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡
 
በአወል አበራ
Exit mobile version