አዲሰ አበባ፣መጋቢት 26፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዳካርና በርሊን በተካሄዱ ዓለም አቀፍ የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ጉባኤዎች ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ያላትን በጋራ የመልማት መርህ ማስተዋወቅ መቻሉን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ በሴኔጋል ዳካር በተካሄደው 9ኛው የዓለም የውሃ ፎረም እና ጀርመን በርሊን በተካሄደው 8ኛው ኢነርጂ ሽግግር ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያን ተሳትፎ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
ሚኒስትሩ በዚህን ወቅት በጉባኤዎቹ ኢትዮጵያ ለታዳሽ ኃይል የሰጠችውን ትኩረትና በጋራ የመጠቀም መርህ ማስተዋወቅ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በሴኔጋል ዳካር በተካሄደው ፎረም በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተመራው የአመራርና የባለሙያዎች ልዑክ ውጤታማ ስራ ማከናወኑን ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ የውሃ ልማት ስራዎችና የቀጣይ እቅዶች ላይ ማብራሪያ መስጠታቸውንም አንስተው፥ ከዚህ አኳያ ፎረሙ የኢትዮጵያን በጋራ የመልማት ፍላጎት ለማስገንዘብ እድል የፈጠረ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም በፎረሙ በአብነት መነሳቱን ነው ያወሱት፡፡
በጀርመኗ መዲና በርሊን በተካሄደው የ8ኛው የኢነርጂ ሽግግር ጉባኤ ላይም ኢትዮጵያ ንቁ ተሳትፎ አድርጋ መመለሷን ሚኒስትሩ ገልጸው፥ በፎረሙ ኢትዮጵያ በኢነርጂ ዘርፍ ያላትን ከፍተኛ የመልማት አቅምና ፍላጎት ማሳየት ያስቻለ ስኬታማ ውይይት መከናወኑን አስረድተዋል።
በፎረሙ በታዳሽ ሃይል ልማት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባም ስምምነት ላይ መደረሱንም ነው ያነሱት፡፡
በፎረሙ በተደረገ ገለፃም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ታዳሽ ኃይል ዘርፍ እያከናወነችው ያለው ልማት በጥሩ ምሳሌነት ተነስቷል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በፎረሙ ኢትዮጵያ በኢነርጂው ዘርፍ ያላትን የማልማት ፍላጎት በማስተዋወቅ በዘርፉ ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ አካላት ግንዛቤ የተፈጠረበት አጋጣሚ እንደነበርም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም አቋሟን በማጎልበት አፍሪካን በኃይል ለማስተሳሰር እያደረገች የምትገኘውን እንቅስቃሴ ማስረዳት መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!