Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከአብዬ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ኢትዮጵያዊነትን አስቀድመው ወደ አገራችው ለተመለሱ የትግራይ ተወላጅ የሰራዊት አባላት ምስጋና ቀረበ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአብዬ አለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ኢትዮጵያዊነትን አስቀድመው ወደ ሀገራችው ለተመለሱ የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ክብር እና ምስጋና እንደሚገባቸው ተገልጿል።

የመከላከያ ሰላም ማስከበበር ማዕከል ከአብዬ ለተመለሱ ሰላም አስከባሪ አባላት በሁርሶ ኮንተንጀንት ማሰልጠኛ ት/ቤት አቀባበል ያደረገ ሲሆን÷ ስለነበራቸው ግዳጅ አፈፃፀም እና ቀጣይ በሚጠብቃቸው ሀገራዊ ተልዕኮ ዙሪያም ውይይት ተካሂዷል።

ውይይቱን የመሩት በመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል የሎጀስቲክስ መምሪያ ኃላፊው ብ/ጀኔራል ጠቅለው ክብረት ÷ ሀገራችሁን ወክላችሁ በአብዬ የነበራችሁን አለም አቀፍ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ በድል በመወጣት የሀገራችን ስም ከፍ ብሎ እንዲጠራ አድርጋችኋል፤ ምስጋናም ይገባችኋል ብለዋል።

ብ/ጀኔራል ጠቅለው የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የሰራዊት አባላት ወደ ሀገራቸው እንዳይመለሱ በሀገር ውስጥ እና በውጭ በሚገኙ አፍራሽ ሀይሎችና በሴረኞች ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሳይበገሩ ኢትዮጵያን አስቀድመው በመምጣታቸው በሰላም ማስከበር ማዕከል እና በመከላከያ ስም ያላቸውን ክብርና ምስጋና ገልጸዋል።

አፍራሽ ኃይሎች ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ የትግራይ ተወላጅ የሰራዊት አባላትን ታስረዋል፣ ተገድለዋል የሚል መረጃ በማህበራዊ ድረ ገፅ የለቀቁ መሆኑን የገለፁት ጀኔራል መኮንኑ መረጃው ሙሉ በሙሉ ሀሰተኛ እና በሴራ የተቀነባበረ ነው ብለዋል።

ጀነራል መኮንኑ መከላከያ እንደሌሎች ሰላም አስከባሪ ሰራዊት አባላት ሁሉ ከሰላም ማስከበር ተልዕኮ የሚመለሱ የትግራይ ተወላጅ የሰራዊት አባላትን መብት እና ጥቅም የማክበር ግዴታ እና ኃላፊነት እንዳለበትም ተናግረዋል።

ጀነራል መኮንኑ አያይዘውም በሀገር ውስጥ ከነበረው ግጭት ጋር በተያያዘ ከሰላም ማስከበር ለተመለሱ አባላት ማብራሪያ መስጠታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ፌስ ቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በህግ ማስከበርና በህልውና ዘመቻ እንዲሁም በዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት ወቅት ሰራዎታችን አሸባሪውን ህወሓትና ጀሌዎቹን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት በሀገር ላይ የተደቀነውን አደጋ መቀልበስ መቻሉን የገለፁ ሲሆን÷የኢትዮጵያ ህዝብም ልጆቹን መርቆ መከላከያን እንዲቀላቀሉ ከማድረግ ጀምሮ በሞራል፣ በገንዘብ እና በአይነት ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና አገራችን የሰጡንን አደራ ጠብቀን እርስ በዕርስ በመደጋገፍ በአብዬ የነበረንን ዓለም አቀፍ ተልዕኮ በብቃት ፈፅመናል ያሉት የሰላም አስከባሪ አባላቱ÷በቀጣይም መከላከያ በሚመድባቸው የግዳጅ ቀጠና ሁሉ ለሀገራቸው ሰላም ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የተደረገልን አቀባበል ከጠበቅነው በላይ ነው ያሉት የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ ሰራዊት አባላት÷አገር አደራ ሰጥታ እንደላከችን እኛም በክብር ወደ ሀገራችን ተመልሰናል ብለዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version