Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ዩክሬን ለሩሲያ ግልጽ ጠላት መሆኗን አሳይታለች-ዲሚትሪ ፔስኮቭ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዘመናዊቷ ዩክሬን የሩሲያ የረጅም ጊዜ ጠላት መሆኗን አሳይታለች ሲሉ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ተናገሩ፡፡

ቃል አቀባዩ ለቤላሩስ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደተናገሩት÷ ዩክሬን ለእኛ የደህንነት እና ህልውና ስጋት የሆነች ሀገር ናት፤አሁን ላይ ደግሞ ግልፅ ጠላትነቷን አሳይታለች፡፡

ዩክሬን ባለፉት በርካታ ዓመታት በቀደምት ሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦች እና የሩሲያ ሚዲያዎች ላይ የጥላቻ ቅስቀሳዎችን ስታስተላለፍ መቆየቷን እና ኒዮ ናዚ ምዕራባውያን አገራትን ወዳጆቿ አድርጋ መቆየቷን አብራርተዋል፡፡

ዩክሬን ናዚዎችን ወዳጅ ያደረገች ፣ የሩሲያን ሚዲያዎች ሙሉ በሙሉ ያገደች እና የሩሲያን ቋንቋ ከስራ ቋንቋነት ያገደች ግልፅ የሩሲያ እና ሩሲያውያን ጠላት አገር ናት ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡

ምዕራባውያን በስደተኞች ላይ የዘርኝነት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያለማንም ከልካይነት እንደሚፈፅሙ የተናገሩት ፔስኮቭ÷ የምዕራበውያንን ግፎች ከሚደበቁላቸው ሀገራት አንዷ ዩክሬን መሆኗንም ጠቅሰዋል፡

ኪየቭ በግልፅ የኒዮ-ናዚ ቡድኖችን ወዳጅ ከማድረግ በተጨማሪ መሰል አመለካከቶችን የሚጋሩ ሰዎችን ከአገሪቱ የኃይል መዋቅር ጋር ግንኙነት እንዲኖራቸው ማድረጓንም ጠቁመዋል፡፡

ዩክሬን በዩናይትድ ስቴትስ የሚመራውን የኔቶ ጥምረት በህገ መንግስቷ ውስጥ ለማካተት ፍለጎት እንደነበራት የተናገሩት ቃል አቀባዩ÷ የኪየቭ ኔቶ ጥምረት ለሞስኮ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ሆኖ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡

ዩክሬን በቀጣይ አሁን ያለውን ሁኔታ እንደምታስተካክል እና ለሩሲያ እና ለራሷ ህዝብ የጠላት አካል መሆኗን እንደምታቆም ተስፋ እናደርጋለንም ብለዋል፡፡

ሩሲያ አሁንም ዩክሬን ራሷን ገለልተኛ አገር መሆኗን በይፋ እንድታውጅ ትጠይቃለች ፤በጭራሽ የኔቶ ህብረትን እንድትቀላቀል አንፈቅድም ያሉት ቃል አቀባዩ÷ የወታደራዊ ዘመቻው ዋና አላማም የዩክሬንን የጦር መሳሪያ ማውድም እንጅ ዩክሬንን እንዳልሆነ መግለጻቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version