Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ሰላም የምታደርገውንድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ተጠየቀች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ሰላም እና መረጋጋት የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ተጠይቃለች፡፡
 
በኢፌዲሪ የሀገር መከላከያ ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም በላይ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የተላከ መልዕክት ለደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት አድርሷል።
ዶ/ር አብርሃም በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ከደቡብ ሱዳን ሰላም ስምምነት አተገባበር ጋር ተያይዞ ከሰሞኑ በአገሪቱ የተከሰተው ውጥረት ያሳሰበው መሆኑን በመግለጽ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።
 
ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት በበኩላቸው ኢትዮጵያ ሁሌም ቢሆን ለደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋት ቀዳሚ ሚና ስትጫወት የቆየች አገር መሆንዋን በማውሳት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ወቅት መልዕክተኛ መላካቸውን አድንቀዋል።
 
ከሰሞኑ በአገሪቱ የታየው ሁኔታ በአግባቡ መያዙን ገልጸው÷ በመተግበር ላይ ያለው ስምምነት ውስብስብ ባህሪያት ያሉት በመሆኑ አልፎ አልፎ መሰል ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
 
ከዚህ በተጨማሪ የሰላም ስምምነቱ ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ ለልዑካን ቡድኑ አስረድተዋል።
 
በተመሳሳይ የኢፌዲሪ የሀገር መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ከተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳነት ዶክተር ሪክ ማቻር ጋር ውይይት አድርገዋል።
 
በወቅቱ ዶክተር ሪክ ማቻር ኢትዮጵያ አሁን በመተግበር ላይ ያለው የሰላም ስምምነት እንዲፈረም የመሪነት ሚና መጫወቷን በማስታወስ ድጋፏን አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።
 
በዶ/ር አብርሃም የተመራው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በጁባ ቆይታው የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት አፈጻጸምን በመደገፍና በመቆጣጠር ተግባር ላይ ከተሰማሩ የተለያዩ ድርጅቶች ኃላፊዎች ጋርም መክሯል።
 
በዚሁ መሠረት ልዑኩ ከተ.መ.ድ. የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ፣ ከሰላም ስምምነት አፈጻጸም ተቆጣጣሪ ኮሚሽን እንዲሁም ከተኩስ አቁም ቁጥጥር ኃላፊዎች ጋር በተናጠል ውይይት አድርጓል።
 
ዶ/ር አብርሃም በዚሁ ወቅት ተቋማቱ እያደረጉት ያለውን ገንቢ አስተዋጽኦ በማድነቅ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ አበረታተዋል።
 
የኢትዮጵያ መንግሥት በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ቀደም ሲል የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
 
የተቋማቱ ኃላፊዎች በበኩላቸው ÷ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ በዲፕሎማሲና በሰላም ማስከበር ስታደርግ የቆየችውን ወሳኝ ጥረት በአዲስ መልክ አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።
Exit mobile version