Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሀገርን የሚለውጥ ውጤት ለማምጣት እየተደረገ ላለው ጥረት የኢንተርፕራይዞች ሚና የላቀ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ድህነትን ከመሰረቱ ለማስወገድና ሀገርን የሚለውጥ ውጤት ለማምጣት እየተደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ጥረት ስኬት የኢንተርፕራይዞች ሚና የላቀ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

በኦሮሚያ ክልል 12ኛው ዙር አንቀሳቃሽ ኢንተርፕራይዞችን ወደ መካከለኛ ባለሀብትነት የማሸጋገር ሥነሥርዓት ዛሬ በአዳማ አባ ገዳ አዳራሽ ተካሂዷል።

በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ተደራጅተው በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ስኬታማ በመሆን ወደ መካከለኛ ባለሀብትነት የተሸጋገሩት 740 ኢንተርፕራይዞች ናቸው።

በስነስርዓቱ ላይ ፕሬዚዳንት ሽመልስ “ትንሽ ባስመዘገብነው ውጤት መደሰት ሳይሆን የበለጠ ተግተን በመስራት ከድህነት መውጣት አለብን” ብለዋል።

አመለካከት፣ ተስፋ መቁረጥና ጠንክሮ አለመስራት የዘርፉ ችግር ሊሆኑ እንደሚችሉም አስገንዝበው ጠንክሮ በመስራት የፋይናንስ ችግርን መወጣት እንደሚቻል ገልጸዋል።

ወደ መካከለኛ ባለሀብትነት የተሻገሩት ኢንተርፕራይዞች መቆጠብና መበደር እንዲችሉ ስንቄ ባንክ በ7 ቢሊዮን ብር መቋቋሙን አስታውሰዋል።

ትልቁ ስኬት በመቶዎች የሚቆጠሩ አንቀሳቃሾችን ማሻገር ሳይሆን በስራቸው የሚፈጥሩት የስራ እድል መሆኑን ገልጸው፤ “ያን ማድረግ ስንችል 10 ሺዎችን ማሻገር እንችላለን” ብለዋል።

ዕውቅና አግኝተው ወደ ቀጣይ ባለሃብት የተሸጋገሩት ኢንተርፕራይዞች “በፈተና ውስጥ ስኬት ያስመዘገቡ ጀግኖች ናቸው” ያሉት ደግሞ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የከተማ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ ናቸው።

የክልሉ መንግሥት በመደበኛነት ለዜጎች ከሚፈጥረው የስራ ዕድል በተጨማሪ የግሉን ዘርፍ በመደገፍና በማበረታታት ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም ኢዜአ ዘግቧል።

 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version