Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በሰላም እጦት ትምህርታቸውን አቋርጠው የነበሩ ተማሪዎችን አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ከአክሱም፣ ከዲግራትና ከወልድያ ዩኒቨርሲቲዎች በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ከነበሩ 726 ተማሪዎች መካከል 270 ያህሉ በዛሬው ዕለት ተመርቀዋል።
 
በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ግጭትና ጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው ትምህርታቸውን መከታተል ያልቻሉ ተማሪዎችን ትምህርት ሚኒስቴር ወደ ተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመመደብ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረጉ ይታወሳል።
 
በዚህ መሰረትም በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ 726 የሚደርሱ ተማሪዎች ተመድበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ።
 
በዛሬው ዕለትም ከአክሱም፣ አዲግራትና ወልዲያ ዩቨርሲቲዎች በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ 270 የሚሆኑ ተማሪዎችም ተመርቀዋል፡፡
 
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ደአ እንደገለጹት÷በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎች ቀጣይ ህይወታቸው እንዳይጨልም በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ እንዲቀጥሉ ተደርጓል።
 
ይህንን ምረቃ ለየት የሚያደርገውም በአገራችን ኢትዮጵያ ላይ ከሀገር ውስጥና ከውጪ አንድነታችንን ለማፍረስ የተቃጣው ሀሳብ በከሸፋበት ማግስት መከናወኑ ነው ብለዋል።
 
በአበበች ኬሻሞና በመለሰ ታደለ
Exit mobile version