Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በድርቅ ለተጎዱ እና ለተፈናቀሉ ዜጎች 9 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ለተፈናቀሉ ወገኖች እና በሶማሌ ክልል በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች 9 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ፡፡
የስደተኞችና ተመላሾች ኮሚሽን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሚገኙ ተፈናቃይ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚውል የ8 ሚሊየን ብር ግምት ያለዉ የአልባሳት፣ የህክምና ቁሳቁስና ተያያዥ ድጋፎች አበርክቷል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን÷ የስደተኞችና ተመላሾች ኮሚሽን ከክልሉ መንግስት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸው፥ ለተፈናቃዮች ላደረገው የዓይነት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች ከቀዬያቸዉ ተፈናቅለዉ በአስቸጋሪ ሁኔታ ዉስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለማቋቋም የበኩሉን ጥረት እያረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትም የድርሻቸውን ትብብርና እገዛ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት የስደተኞችና ተመላሾች ኮሚሽን ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ፥ በክልሉ ከ70 ሺህ በላይ ስደተኞችን የያዙ 5 የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች እንዳሉም ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የሚኖሩ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ተወካዮች በክልሉ በድርቅ ለተጎዱ ነዋሪዎች የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርገዋል።
የተደረገውን ድጋፍ ለድርቁ ምላሽ ለመስጠት በጅግጅጋ ከተማ የተቋቋመው የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ለሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ አስረክቧል።
ድጋፉን የተረከቡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ባደረጉት ንግግር፥ ለድጋፉ ምስጋና አቅርበው የከተማው ነዋሪዎች ህዝቡ ዕርዳታ በሚፈልግበት ወቅት ያደረጉት ድጋፍ ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው ብለዋል።
ነዋሪዎቹ ያደረጉት ድጋፍ በህዝቡ መካከል ያለውን አንድነትና የቆየ የመረዳዳት እሴቶችን የሚያሳይ በመሆኑ እንደዚህ ዓይነት መልካም ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ማለታቸውን ከየክልሎቹ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮዎች ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
Exit mobile version