አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ በበጋ መስኖ 442 ሄክታር ማሳ በስንዴ ማልማት መቻሉን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ አስታወቀ።
የክልሉ ምክር ቤት አባላት በካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ የለማውን የበጋ መስኖ ስንዴ ማሳ ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ፤ በሀገር ደረጃ በምግብ እህል ፍላጎትን በራስ አቅም ለማሟላት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የክልሉን የግብርና ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘንድሮ የበጋ ስንዴ ለማልማት በተደረገው ጥረት 442 ሄክታር ማሳ መሸፈን ተችሏል ብለዋል።
መሬት ጾም የሚያድረበት ጊዜ እንዳይኖር ከበልግና መኸር በተጨማሪ መስኖን በመጠቀም በበጋ ወቅት መስራት አስፈላጊ በመሆኑ ለአርሶ አደሩ ምቹ ሁኔታዎን በመፍጠር ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፤ ሀገራዊ የትኩረት አቅጣጫን ተከትሎ በክልሉ ወደ ስንዴ ልማት እንደተገባ አስታውቀዋል።
በክልሉ በአጠቃላይ በዘር ከተሸፈነው 442 ሄክታር ማሳ 15 ሺህ 470 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም አስረድተዋል።
የምክር ቤቱ አባላት ለመጀመሪያ ጊዜ በሃማኒ ቀበሌ በ15 ሄክታር ማሳ ላይ የለማውን የበጋ መስኖ ስንዴ መጎብኘታቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመልክታል።
በሃማኒ ቀበሌ በመስኖ ስንዴ ካለሙ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ፍቅሬ ወንድሙ በሰጡት አስተያየት፤ ባልተለመደ መልኩ መስኖን በመጠቀም ስንዴ በማልማት ባዩት የምርት አያያዝ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
አሁን ያለሙት ስንዴ ከ15 ቀናት በኋላ ምርቱ እንደሚሰበሰብ ጠቅሰው ፤በቀጣይ ዓመት በበጋ መስኖ ሁለት ጊዜ ለማልማት ማቀዳቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!